የመስኖ ልማት ሲገጥመን የነበረውን የመኖ እጥረት ችግር ቀርፎልናል -የዳሰነች ወረዳ አርብቶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የመስኖ ልማት ሲገጥመን የነበረውን የመኖ እጥረት ችግር ቀርፎልናል -የዳሰነች ወረዳ አርብቶ አደሮች
ጂንካ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):-በመስኖ ታግዘው የጀመሩት የእንስሳት መኖ ልማት ሲገጥማቸው የነበረውን የመኖ እጥረት ችግር እንደቀረፈላቸው በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ አርብቶ አደሮች ገለጹ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ አርብቶ አደሮች መስኖን ተጠቅመው እያለሙት ባለው የተሻሻለ የእንስሳት መኖ ከዚህ ቀደም ሲያጋጥጥም የነበረው የመኖ እጥረት እየተፈታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቦርኮኖች ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ ናማዴ አርዴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ቀደም ሲል በአካባቢው በሚከሰት ድርቅ የእንስሳት መኖ እጥረት ያጋጥም ነበር።
እጥረቱ በሚከሰትበት ወቅት መንግስት መኖ ከሌላ አካባቢ በማምጣት ድጋፍ ያደርግ እንደነበር ጠቅሰው ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት በአካባቢያችን መኖ እንድናለማ ተደርጓል ብለዋል።
በመስኖ ታግዘው በ5 ሄክታር ኩታ ገጠም መሬት ላይ የጀመሩት የእንስሳት መኖ ልማት የመኖ ችግራቸውን ከመፍታት ባለፈ ከመኖ ሽያጭ ተጨማሪ ገቢ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል ።
ከዚህ ቀደም በአካባቢው ድርቅ በተከሰተበት ወቅት የግጦሽ ሣር ፍለጋ ሲንቀሳቀሱ አላስፈላጊ እንግልት ይገጥማቸው እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ በወረዳው የራቴ ቀበሌ ነዋሪ ፔሬ ሎኮሮም ናቸው።
አሁን ላይ በመንግሥት ድጋፍ በመስኖ በመታገዝ በአካባቢው መኖ ማልማት በመጀመራቸው ችግሩ እንደተቀረፈ ገልፀው የመኖ ልማቱ ለከብቶቻቸው ዋስትና መሆኑን ተናግረዋል።
የዳሰነች ወረዳ ግብርና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ፍቅረማርያም አይመላ፤ የአርብቶ አደሮችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ሰፋፊ የግብርና ልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።
ከሰብል ምርት ባሻገር አርብቶ አደሮች በአካባቢያቸው ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ያላቸውን የመኖ ዝርያዎች በማልማትና እንስሳትን በመመገብ የተሻለ ጥቅም እንዲያገኙ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አርብቶ አደሩ ጥራትን መሰረት ያደረገ የእንስሳት እርባታ ዘዴን እንዲከተል በማድረግ የእንስሳት እርባታውን ለማዘመን ትኩረት ተሰጥቷል ብለዋል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መስኖና ቆላማ አካባቢ ልማት ቢሮ የቆላማ አካባቢ ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት፣ የእንስሳት ሃብት ልማት ባለሙያ ዶክተር ይብራህ ገብረመስቀል በበኩላቸው፤ በክልሉ ቆላማ አካባቢዎች ኑሮ ማሻሻያ ፕሮጀክት አማካኝነት በወረዳው ሁለት ቀበሌዎች በሙከራ ደረጃ የተሻለ የመኖ ዝርያ የማስተዋወቅ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
ዝርያው ድርቅን መቋቋም የሚችልና ከፍተኛ የፕሮቲን ይዘት ያለው መሆኑን ጠቅሰዋል።
በመኩራ ደረጃ በሁለት ቀበሌዎች በ10 ሄክታር መሬት ላይ እየለማ ያለው የመኖ ዝርያው ውጤታማ መሆኑን አንስተው፥ በቀጣይም በሌሎች ወረዳዎች ተሞክሮውን ለማስፋት ይሰራል ብለዋል።