በሸገር ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መዘመኑ የህብረተሰቡን እርካታ አሳድጓል - ኢዜአ አማርኛ
በሸገር ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መዘመኑ የህብረተሰቡን እርካታ አሳድጓል
ሸገር፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- በሸገር ከተማ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አሰጣጥን በዘመናዊ መልኩ በማደራጀት፣ የነዋሪዎችን የአገልግሎት እርካታ ደረጃ ማሳደግ መቻሉ ተገለጸ።
በሸገር ከተማ የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተትን በዘላቂነት ለመቅረፍ የአንድ ማዕከል አሰራርን ማስፋፋትና ማዘመን እንደ ዋነኛ የሪፎርም ስራ ተይዞ ሲከናወን ቆይቷል።
የከተማው የአንድ ማዕከል አገልግሎት ሥራ አስኪያጅ አቶ መኮንን አምቤ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ አሰራሩን ማዘመን ፈጣንና ጥራት ያለው ማህበረሰብ ተኮር አገልግሎትን በተግባር ለማረጋገጥ ማስቻሉን ገልጸዋል።
የአገልግሎቱ ዋና ዓላማ የተገልጋዮችን እንግልትና አድካሚ ምልልስ ማስቀረት መሆኑን የገለጹት ሥራ አስኪያጁ፤ አሰራሩ ምቹና ተደራሽ የሥራ ካባቢ በመፍጠር ማህበረሰቡ ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ ማስቻሉን አስረድተዋል።
በተለይም የአገልግሎት አሰጣጡን በቴክኖሎጂ በመደገፍ ወጪን መቀነስ፣ ለደንበኞች ምቹ ሁኔታን መፍጠር እና የተጠቃሚዎችን እርካታ ማሳደግ መቻሉን ገልጸው፤ ይህም ማህበረሰቡ በመንግስት ላይ ያለው እምነት ከፍተኛ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ያደርጋል ብለዋል።
አገልግሎቱን ይበልጥ ተደራሽና ፈጣን ለማድረግ በሶስት ዋና ዋና መንገዶች ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም አክለው ገልጸዋል።
ይህንን ተግባር ይበልጥ ስኬታማ ለማድረግም የአገልግሎት ማዕከላትን ማስፋፋት ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ሲሆን፤ በዚህ ዓመት ብቻ ሶስት አዳዲስ ማዕከላት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መደረጋቸውን ተናግረዋል።
ወደ ማዕከሉ በመምጣት አገልግሎት ያገኙ ደንበኞች በበኩላቸው፤ በአንድ ማዕከል የሚሰጠው አገልግሎት ከአላስፈላጊ የወጪና የጊዜ ብክነት እንዳዳናቸው ገልጸዋል።
ከተጠቃሚዎች መካከል አቶ መሳይ ተሾመ፤ ቀደም ሲል አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም በተለያዩ ቦታዎች በመመላለስ ጊዜያቸው ይባክን እንደነበር አስታውሰው፣ በአሁኑ ወቅት ግን ጉዳያቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ እየተጠናቀቀላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አቶ ጀማል መሀመድ በበኩላቸው፤ በዚህ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አማካኝነት ያለምንም እንግልትና ምልልስ የሚፈልጉትን አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ ማግኘት መቻላቸውን ገልጸዋል።