የሕክምና ማዕከሉ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል - ኢዜአ አማርኛ
የሕክምና ማዕከሉ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):-"አዲስ የላቀ የሕክምና ማዕከል" ዘመናዊና ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎትን ይበልጥ ተደራሽ ለማድረግ ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዛሬው ዕለት የራስ ደስታ ዳምጠው ሆስፒታል ማስፋፊያ የሆነውን "አዲስ የላቀ የህክምና ማዕከል"ን መርቀው ስራ አስጀምረዋል።
በምረቃው ወቅት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ባደረጉት ንግግር፤ ፕሮጀክቶችን በታቀደላቸው ጊዜ ጀምሮና በፍጥነት አጠናቆ ለአገልግሎት ማብቃት የከተማ አስተዳደሩ መለያ ባህል መሆኑን ገልጸዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ ከሠራባቸው ማኅበራዊ ዘርፎች መካከል የጤናው ዘርፍ ተጠቃሽ መሆኑንም አክለዋል።
በመዲናዋ የነበረውን የጤና አገልግሎት ለማሻሻል የበርካታ አዳዲስ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ግንባታ መከናወኑን የጠቀሱት ከንቲባዋ፤ ከአዳዲስ ግንባታዎች ባሻገር በነባር የጤና ተቋማት ላይ ሰፊ የማስፋፊያና የእድሳት ሥራዎች መሠራታቸውን አስታውቀዋል።
ይህም ለሕብረተሰቡ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ትርጉም ያለው ለውጥ ማምጣቱን አመላክተዋል።
ከዚህ ቀደም ዜጎች በከፍተኛ ወጪ ወደ ውጭ ሀገር ሄደው ያገኟቸው የነበሩ የሕክምና አገልግሎቶች አሁን ላይ በከተማዋ መሰጠት መጀመራቸው ሀገሪቱን ከውጭ ምንዛሬና ዜጎችን ደግሞ ከእንግልት መታደጉን ጠቁመዋል፡፡
በጤናው ዘርፍ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ ተግባራት አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል እንድትሆን እያደረጋት እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ዛሬ ተመርቆ ለአገልግሎት የበቃው "አዲስ የላቀ ሕክምና ማዕከል" የሆስፒታሉን የአገልግሎት አሰጣጥ አድማስ በማስፋት፣ ለተገልጋዮች ምቹና ዘመናዊ ሆኖ መደራጀቱን ጠቅሰዋል፡፡
ማዕከሉ የራሱ የኦክስጅን ማምረቻን ጨምሮ ዘመኑን በዋጁ ልዩ ልዩ ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች የተደራጀ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ ቀደም የነበረውን ዘመናዊ እና ጥራቱን የጠበቀ የሕክምና አገልግሎት ይበልጥ ለማላቅና አቅምን ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ብለዋል።
የማስፋፊያ ማዕከሉ ባለ ሰባት ወለል ሲሆን በ2 ሺህ 60 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ነው፡፡