በክልሉ ለመስኖ ልማት የተሰጠው ትኩረት በድርቅ ተጠቂ የነበሩ አከባቢዎችን ወደ አምራችነት አሸጋግሯል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ ለመስኖ ልማት የተሰጠው ትኩረት በድርቅ ተጠቂ የነበሩ አከባቢዎችን ወደ አምራችነት አሸጋግሯል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):-በኦሮሚያ ክልል ለመስኖ ልማት የተሰጠው ትኩረት በድርቅ ተጠቂ የነበሩ አከባቢዎችን ወደ አምራችነት ማሸጋገሩን የኦሮሚያ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ በሪሶ ፈይሳ ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም ዘንድሮ በኩታ ገጠም፣ በመስኖና በቴክኖሎጂ ታግዞ በለማ 29 ሚሊዮን ሄክታር መሬት 1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ኩንታል ምርት መገኘቱን ገልጸዋል፡፡
ቀደም ሲል በድርቅ ይፈተን የነበረው የቦረና አካባቢ በአሁኑ ወቅት በስንዴ ልማት ያሳየውን ስኬት በዋነኛ ማሳያነት አንስተዋል።
የኦሮሚያ ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ የሆኑት አቶ በሪሶ ፈይሳ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ በክልሉ የተዘረጉ ዘመናዊ አሠራሮች፣ የተሳለጠ የግብዓት አቅርቦት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር የግብርናውን ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንዳሸጋገሩት ገልጸዋል።
ባለፉት ዓመታት በባህላዊ መሣሪያዎች ላይ ብቻ ተደግፎ የነበረውን ግብርና ወደ መካናይዜሽን እየተሸጋገረ መሆኑ ትልቅ እምርታ ያመጣ ስትራቴጂካዊ እርምጃ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመካናይዜሽን መስፋፋት አርሶ አደሩን ከዕለታዊ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ የሚሆን ምርት በስፋት እንዲያመርትና ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲሸጋገር በር ከፍቶለታል ብለዋል።
በክልሉ በስፋት ተግባራዊ የተደረገው የኩታ ገጠም የእርሻ ሥርዓት፣ ይፋ የተደረጉ ግብዓቶችና የመካናይዜሽን ቴክኖሎጂዎችን በአንድ ቋት ውስጥ በጥምረት ለመጠቀም ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
በክልሉ በስፋት የተተገበረው የኩታ ገጠም የስንዴ ልማት በበጋ መስኖ፣ በመኸር እና በበልግ ወቅቶች በተከናወኑ የተቀናጁ የልማት ሥራዎች፤ ከ6 ነጥብ 8 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ3 መቶ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ማምረት መቻሉን ጠቁመዋል፡፡
ይህ ውጤት የክልሉ ግብርና እየተመራበት ያለው አዲስ አቅጣጫ ውጤታማና ተስፋ ሰጪ ለመሆኑ ትልቅ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ቀደም ሲል በከፍተኛ ድርቅ ይታወቁ የነበሩ ቆላማ አካባቢዎችን ቀጣይነት ወዳለው አምራችነት ለመቀየር የተከናወኑት ተግባራት የዘርፉ ትልቅ ስኬቶች ናቸው ብለዋል።
በተለይም በቦረና ዞን ወደ ሥራ የገቡት የፊና መስኖ ግድብና መሰል ፕሮጀክቶች የማኅበረሰቡን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት በተግባር አረጋግጠዋል ብለዋል።
የመስኖ ፕሮጀክቶቹ አርብቶ አደሩ ማኅበረሰብ ለዘመናት ለውኃና ለሳር ፍለጋ ከቦታ ወደ ቦታ ያደርግ የነበረውን ስደትና ባህላዊ የሕይወት ዘይቤ ከመሠረቱ መለወጣቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ ስትራቴጂካዊ ሥራዎች በአካባቢው ላይ የነበረውን እይታ በመቀየር፣ ዛሬ ላይ ቆላማ አካባቢዎች የሰፊ የስንዴ ልማትና የመስኖ ማዕከል እንዲሆኑ ማስቻሉንም ጠቁመዋል፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሳሽነት ተግባራዊ የተደረገው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር በክልሉ ባሉ ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ሁሉ በስፋትና በተቀናጀ ሁኔታ እየተተገበረ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።
የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ በሥርዓተ-ምግብና በኢኮኖሚው ዘርፍ ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት ላይ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም በዶሮ ሥጋ፣ በእንቁላል፣ በወተትና በማር ምርት ከፍተኛ እምረታ መምጣቱን ጠቅሰው የተሻሻሉ የወተት ላሞች ዝርያ አቅርቦት እና የመኖ ልማት ሥራዎች በትይዩ በመከናወናቸው የወተት ምርት በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ጠቁመዋል፡፡
ይህ ስኬት የአርሶ አደሩ የገቢ ምንጭ እንዲሰፋና ጤናማ ማኅበረሰብ እንዲገነባ ትልቅ አቅም መሆኑንም ጠቁመው መርሐ ግብሩ ገበያን ከማረጋጋት ባለፈ ለበርካታ ዜጎች የሥራ እድል መፍጠር መቻሉንም አብራርተዋል፡፡