ወደ እፎይታ የተሸጋገሩ የአዲስ አበባ ነፍሶች - ኢዜአ አማርኛ
ወደ እፎይታ የተሸጋገሩ የአዲስ አበባ ነፍሶች
በተስፋ ሰብዓዊነት ሰገነት ታጅበው፤ ወደ እፎይታ የተሸጋገሩ የአዲስ አበባ ነፍሶች
ዝናብ ለብዙ ሰዎች የተፈጥሮ ውበት ነው። ለሌሎች ደግሞ የሰብል ተስፋ፣ የምድር ሕይወትና የአረንጓዴ ወቅት መገለጫ ነው። በአዲስ አበባ አንዳንድ ሰፈሮች ዝናብ ለቤተሰቦች የእፎይታ ሳይሆን የስጋት ምንጭ ነበር። የሚያፈሱ ጣሪያዎች፣ የተሰነጣጠቁ ግድግዳዎች፣ በውኃ የሚጥለቀለቁ ወለሎችና በአደጋ የተከበቡ መኖሪያዎች ለበርካታ ቤተሰቦች የዕለት ተዕለት የጭንቀት ምንጮች ነበሩ።
የክረምት ወቅት ሲመጣ የቤት ዕቃዎችን ከደራሽ ጎርፍ ለመጠበቅ ከቦታ ወደ ቦታ ማንቀሳቀስ፣ ሕፃናት ከብርድና ከእርጥበት እንዲድኑ በርካታ ሌሊቶችን ነቅቶ መጠበቅ፣ የእሳትና የጎርፍ አደጋን በፍርሃት መጠበቅ የኑሯቸው አካል ሆኖ ቆይቷል። አንዳንዶች በየጊዜው በሚከሰቱ የእሳት አደጋዎች ስጋት ውስጥ ይኖሩ ነበር። ሌሎች ደግሞ በወንዝ ዳርቻና በተዳፋት ቦታ ስለሚኖሩ ለጤናና ለደህንነት የሚያሰጋ ሁኔታን በየዕለቱ ይጋፈጡ ነበር። ዛሬ ግን ያ ምስል በብዙ ስፍራዎች ተቀይሯል።
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሪነት በባለሀብቶች፣ በወጣቶች፣ በበጎ ፈቃደኞችና በማህበረሰቡ የጋራ ተሳትፎ የተከናወኑ የቤት ግንባታና የዕድሳት መርሃ ግብሮች ብዙዎችን ከአደገኛ መኖሪያ ወደ ዘመናዊና ምቹ ቤት በማሸጋገር ሰብዓዊ ውጤት እየስገኙ ይገኛል። እነዚህ ፕሮግራሞች የጡብና የሲሚንቶ ሥራ ብቻ አይደሉም። ሰብዓዊ ክብርን የሚያጎናጽፉ፣ ቤተሰቦችን በእፎይታ የሚያኖሩና የሕፃናትን የነገ ተስፋ የሚያለመልሙ ለውጦች ናቸው።
በዚህ ተጠቀሚ ከሆኑ የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል የልደታ ክፍለ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ቤተልሔም አስፋ ይገኙበታል። እርሳቸው እንደሚገልጹት፣ ከዚህ ቀደም የሚኖሩበት ቤት እጅግ ያረጀ፣ በዝናብ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ የሚያፈስና ለኑሮ የማይመች ነበር። መኖሪያ ቤታቸው በወንዝ ዳርቻና በተዳፋት ቦታ ላይ የሚገኝ በመሆኑ ልጆቻቸው ለተለያዩ የጤና ችግሮች ይጋለጡ እንደነበርም ያስታውሳሉ።
በበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሩ አማካኝነት መሠረተ ልማት ወደተሟላለትና ለትራንስፖርት አመቺ ወደሆነ አካባቢ መሸጋገራቸው የቤተሰባቸውን ሕይወት እንደለወጠው ይናገራሉ። ዛሬ የዝናብ ወቅት የፍርሃት ምልክት አይደለም፤ የተረጋጋ ሕይወትን በሚያሳይ አዲስ ምዕራፍ ተተክቷል። ለሰው ልጅ መኖር አዳጋች ከነበረ ቤት ወጥተን ዛሬ በክብር ወደምንኖርበት ቤት ገብተናል፤ ይህ ለእኛ አዲስ የሕይወት ምዕራፍ ነው ይላሉ ወይዘሮዋ።
የወይዘሮ ቤተልሔም ታሪክ ግን ብቸኛ አይደለም፤ በከተማው በበጎ ፈቃድ ፕሮግራም የተጠቀሙ ብዙ ቤተሰቦች ተመሳሳይ የአኗኗር ለውጥ ታሪክ ባለቤት ናቸው። በከተማው እየተከናወኑ በሚገኙ በጎ ፈቃድ መርሃ ግብሮች ተጠቃሚ የሆኑ በርካታ ዜጎች በሕይወታቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ መጥቷል።
ወይዘሮ ገነት ወልደማርያም ያለፉትን ዓመታት ሲያስታውሱ በጠባብና ለኑሮ በማይመች አካባቢ መኖር ለቤተሰባቸው በየቀኑ የሚደገም ፈተና እንደነበር ይናገራሉ። መተላለፊያ የሌለው፣ መሠረተ ልማት ያልተሟላለትና ለልጆች ዕድገት በማይመች አካባቢ ሕይወታቸውን አስቸጋሪ አድርጎት እንደነበር ያስታውሳሉ።
ዛሬ ግን በመንግሥትና በበጎ ፈቃደኞች ትብብር የተገነባላቸው አዲስ መኖሪያ ቤት ከመጠለያነት ባለፈ ለቤተሰባቸው አዲስ የሕይወት ጅማሬ ሆኗል። በደህንነት የሚያድሩበት፣ በክብር የሚኖሩበትና ልጃቸው ያለ ፍርሃት የሚያድግበት ቤት ማግኘታቸውን በትልቅ የህይወት ስጦታነት ይገልጹታል።
ይህ የቤት ግንባታ ፕሮግራም የግለሰብ ሕይወትን ብቻ የሚቀይር አይደለም። የቤተሰብ መረጋጋትን፣ የጎረቤት ትስስርንና የማህበረሰብ አንድነትን የሚያጠናክር ሰብዓዊ ኢንቨስትመንት መሆኑን የተጠቃሚዎቹ ታሪክ ያስረዳል።
የተገነባው ቤት ብቻ አይደለም፤ ተስፋችንም ነው የሚሉት ደግሞ ሌላኛው የበጎ ፈቃድ ዘመናዊ መኖሪያ መንደር ግንባታ ተጠቃሚ የሆኑት ሀርቆ ሀለጮ ናቸው። በመንግሥትና በበጎ ፈቃደኞች ትብብር የተደረገላቸው ድጋፍ ሕይወታቸውን እንደለወጠው ይናገራሉ። ለእርሳቸው የተገነባው ቤት የመጠለያ ቦታ ብቻ ሳይሆን፣ ማህበረሰቡ ከጎናቸው መቆሙን የሚያሳይ የክብር ማህተም ነው።
የአቶ ሀርቆ ሀለጮ ታሪክ የሚያመለክተው አንድ ጠቃሚ እውነት አለ። ሰብዓዊ ድጋፍ በቁሳዊ እርዳታ ብቻ አይለካም። ተጠቃሚዎች እንደሚገልጹት፣ "እኛን የሚያስብ ማህበረሰብ አለ" የሚል ስሜት እንደተሰማቸውም ነው የሚናገሩት። ይህ ደግሞ ከግንባታው በላይ የሚዘልቅ ግዙፍ ሰብዓዊ ዋጋ አለው።
በተመሳሳይ ወይዘሮ ወጋየሁ ወርቁ የቀድሞ መኖሪያቸው በመጨናነቅና በየጊዜው በሚከሰቱ የእሳት አደጋዎች ስጋት የተሞላ ሕይወት ይመሩ እንደነበር ያስታውሳሉ። አሁን ግን በአዲሱ መኖሪያቸው የሚሰማቸው ስሜት ከፍርሃት ይልቅ መረጋጋት፣ ከጭንቀት ይልቅ ተስፋ ነው።
የእነዚህ ቤተሰቦች ታሪክ በአዲስ አበባ የተከናወኑ የበጎ ፈቃድ ተግባራት የሚለኩት በተገነቡ ቤቶች ብዛት ብቻ ሳይሆን፣ በተለወጡ ሕይወቶች እና በተረጋጉ የአኗኗር ዘይቤዎችም ጭምር መሆኑን በግልጽ ያሳያል። የሰብዓዊነት ባህል ሲደረጅ ከሕንፃ ግንባታ የተሻገረን ትውልድ ያንፃል።
በአዲስ አበባ የተከናወኑና የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ ተግባራት በቤት ግንባታ ብቻ የሚወሰኑ አይደሉም። የከተማዋ የምገባ ማዕከላት በየዕለቱ ለአረጋውያን፣ ለአቅመ ደካሞችና ለሌሎች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች የሚቀርቡ የምግብ ድጋፍ፣ የቤት ዕድሳትና ግንባታ፣ እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ባለቤትነትን የሚያረጋግጡ ፕሮግራሞች በአንድ ላይ ተደምረው ለሺዎች ዜጎች አዲስ የሕይወት ምዕራፍ እየከፈቱ ነው።
በየዓመቱ በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሮች ወጣቶች ጉልበታቸውን፣ ባለሀብቶች ገንዘባቸውን፣ የማህበረሰብ አባላት ጊዜያቸውንና ሙያቸውን በማበርከት ሰብዓዊ አገልግሎትን ከንቅናቄ ወደ ባህል እንዲያድግ አስችለዋል። በዚህም ከቤት ግንባታ ባሻገር የመተሳሰብና የመረዳዳት ዕሴቶች በከተማዋ ይበልጥ እንዲጠናከሩ አድርገዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሕብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አስራት ንጉሴ እንደገለጹት፣ ቀደም ሲል በከፊል የቤት ዕድሳት ላይ ያተኮረው አሠራር በአሁኑ ወቅት የከተማዋን የልማት አቅጣጫ በሚመጥን መልኩ ወደ ሙሉ የቤት ግንባታ ተሸጋግሯል። ይህም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ዜጎች፣ አረጋውያን፣ አካል ጉዳተኞች፣ አቅመ ደካሞችና ወላጅ አልባ ሕፃናት በቀዳሚነት ተጠቃሚ አድርጓል።
በእርግጥም ልማት የሚለካው በሚገነቡ ሕንፃዎች ከፍታ ብቻ አይደለም። በዜጎች ሕይወት ላይ በሚመጣ ለውጥ እንጂ። በበጎ ፈቃድ መርሃ ግብሮች አማካኝነት ከሚያፈሱ ጎጆዎች ወደ ዘመናዊ መኖሪያዎች የተሸጋገሩ ቤተሰቦች፣ በምገባ ማዕከላት የዕለት ምግብ ዋስትና ያገኙ አረጋውያን፣ በተለያዩ ማህበራዊ ፕሮግራሞች ተደግፈው ተስፋን ያገኙ ዜጎች የዚህ እውነታ ሕያው ማሳያዎች ናቸው።
ወይዘሮ ቤተልሔም፣ ወይዘሮ ገነት ወልደማርያም፣ አቶ ሀርቆ ሀለጮና ወይዘሮ ወጋየሁ ወርቁ ያካፈሉን ተሞክሮ የሚያሳየው አንድ ግልጽ መልዕክት ለሰው ልጅ ክብር የሚሰጥ መኖሪያ፣ የተረጋጋ የምግብ ዋስትናና የማህበረሰብ ድጋፍ ሲገናኙ የሚለወጠው ቤት ብቻ አይደለም፤ ሕይወት መሆኑን እንጂ።
ስለዚህ በአዲስ አበባ የሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ ተግባራት ከማህበራዊ ድጋፍ ባለፈ የከተማዋን የሰብዓዊ ልማት አቅጣጫ የሚያንፀባርቁ ናቸው። ከሚያፈስ ጎጆ ወደ ክብር መኖሪያ የተጀመረው ጉዞ፣ የጡብና የሲሚንቶ ታሪክ ሳይሆን የሰውን ክብር የመጠበቅ፣ ተስፋን የማደስና የማህበረሰብ አንድነትን በሚያጠናክር መልኩ እየቀጠለ ይገኛል።