ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የጌዴኦን ባህላዊ መልክዓ ምድር ከጎበኙ ቱሪስቶች 50 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ተገኝቷል

ዲላ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የጌዴኦን ባህላዊ መልክዓ ምድር ከጎበኙ የሀገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች 50 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ መገኘቱን የዞኑ ቱሪዝም መምሪያ ገለጸ።

የመምሪያው ኃላፊ አቶ እድሉ ታደሰ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የዞኑን የቱሪዝም አቅም አሟጦ ለመጠቀም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ደረጃና አገልግሎት በማሻሻል ለጎብኝዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር ተችሏል። 


 

የጌዲኦ ባህላዊ መልክዓ ምድር ያቀፋቸውን ተፈጥሯዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ቱሪስት መሳብ የሚያስችሉ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸውንም ገልጸዋል።

በዚህም በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መልክዓ ምድሩ ከ40 ሺህ በሚበልጡ የውጭና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች መጎብኘቱን ጠቅሰው፣ 50 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢም መገኘቱን አስታውቀዋል።

ገቢው ካለፉት ዓመታት ብልጫ ያለው ሲሆን የቡና ቱሪዝም መስፋፋት፣ የምርምር ስራዎች መጠናከር እንዲሁም በአካባቢው ያለው ሰላም ለገቢው መጨመር ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።

በዞኑ የመዳረሻ ስፍራዎች ልማትን በማጠናከር የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ኃላፊው፤ በኮቾሬ ወረዳ የሚገኘውን የራኮ ተራራ ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል። 

የራኮ ተራራን ውብ ገጽታ በማልማትና በማስተዋወቅ ቱሪስቶችን ለመሳብ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ያነሱት ደግሞ የኮቾሬ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ ዳዊት ጀቦ (ዶ/ር) ናቸው።


 

በተለይም ወደ ተራራው መውጫ መንገድና በተራራው ላይ መቆያ ስፍራ፣ እንዲሁም ሕብረተሰቡን ያሳተፈ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች መከናወናቸውን አንስተዋል። 

ይህም የተራራውን የተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭነት በመቀነስ ለመስህብነቱ ያለው አቅም እንዲጎለበት እያገዘ መሆኑን አስረድተዋል።

የዳራሮ "ሀገርህን እወቅ" ማኅበር ሰብሳቢ መላኩ ታደሰ በበኩላቸው፤ “ሀገርን ማወቅ አካባቢን ከማወቅ ይጀምራል” በሚል መሪ ሐሳብ የጌዴኦ ባህላዊ መልክዓ ምድርን የማወቅና የማስተዋወቅ ሥራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በዚህም የመስህብ ስፍራዎችን በመጎብኘትና በተለያዩ አማራጮች በማስተዋወቅ ቱሪስቶች በስፋት ወደ አካባቢው እንዲመጡ ከመስራት ባለፈ፣ ለጎብኚዎች መረጃ በመስጠት የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማጎልበት እየሰሩ እንደሚገኙም ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም