የአማራ ልማት ማህበር/አልማ/ የህዝብን ጥያቄ መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአማራ ልማት ማህበር/አልማ/ የህዝብን ጥያቄ መሰረት ያደረጉ የልማት ስራዎችን እያከናወነ ነው
ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- የአማራ ልማት ማህበር (አልማ) የህዝብን ጥያቄ መሰረት ያደረጉ ውጤታማ የልማት ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ አስታወቀ።
ማህበሩ ከሐምሌ 1 እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ.ም የሚካሄደውን የአልማ ሳምንትና የ35ኛ ዓመት የምስረታ በዓል አከባበር በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
የማሕበሩ ምክትል ስራ አስፈፃሚ አቶ አበረ መኩሪያ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ አልማ የልማት ፍላጎቶችን በመለየት ውጤታማ ስራዎችን እያከናወነ ይገኛል።
በተለይም በትምህርት፣ በጤና ፣ በስራ ዕድል ፈጠራ፣ በአደጋ ጊዜ ምላሽ በመስጠት እና መልሶ ማቋቋም ስራዎች ላይ ተሳትፎ እያደረገ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።
ማህበሩ ከ2017 እስከ 2021 የሚቆይ ስትራቴጂክ እቅድን ተግባራዊ በማድረግ 3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ሀብት ማሰባሰብ መቻሉን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም 23 ነጥብ 9 ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በመፈራረም እየሰራ ይገኛል ብለዋል።
በዚህም አንድ ሺህ 658 የመማሪያ ክፍሎችን በመገንባት ለአገልግሎት ያበቃ ሲሆን በርካታ የመማሪያ ክፍሎችንም እየተገነቡ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በጤናው ዘርፍም 55 የጤና ኬላዎች ፣ ጤና ጣቢያ እና የህዝብ መድሃኒት ቤቶችን በመገንባት ለአገልግሎት እንዲበቁ ማድረጉን አንስተዋል።
ለስራ እድል ፈጠራ የሚያገለግሉ የመስሪያና የመሸጫ ሼዶችን ገንብቶ ከማስረከብም ባለፈ ለወጣቶች የህይወት ክህሎት ስልጠና በመስጠት ዘርፉን የማጠናከር ስራ መሰራቱን አብራርተዋል።
ማህበሩ በቀጣዩ በጀት ዓመትም የአባላቱን ቁጥር አሁን ካለበት 4 ነጥብ 9 ሚሊዮን ወደ 5 ነጥብ 9 ሚለዮን በማሳደግና ሀብት በማሰባሰብ የልማት ስራዎችን ለማከናወን ማቀዱን አብራርተዋል።
ከሐምሌ 1 ቀን እስከ ሐምሌ 15 ቀን 2018 ዓ.ም ለ7ተኛ ጊዜ የሚከበረው የአልማ ሳምንት ከ35ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉ ጋር ተቀናጅቶ እየተከበረ ይገኛል ብለዋል።
ይህ በየደረጃው የሚከበረው የአልማ ሳምንት የህዝብ ንቅናቄ ለመፍጠር፣ አዳዲስ አባላትን ለማፍራትና ለልማት ስራዎች የሚውል ሃብት ለማሰባሰብ ዓላማ የደረገ ነው ብለዋል።
መርሐግብሩ በጎዳና ላይ ሩጫ፣ በፕሮጀክቶች ምረቃ፣ በችግኝ ተከላ፣ በፓናል ውይይት፣ በፎቶ ኤግዚቢሽንና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ በመስራት ይከበራል።
አልማ እያከናወናቸው የሚገኙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተግባራትን በማጠናከር የህዝብ የልማት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አባላትና ደጋፊዎች ከመቼውም ጊዜ በላቀ ድጋፍና እገዛቸውን እንዲያጠናክሩ ጥሪ አቅርበዋል።