ቀጥታ፡

በምዕራብ ሸዋ ዞን በተያዘው መኸር ከ48 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቢራ ገብስ እየለማ ነው

አምቦ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- በምዕራብ ሸዋ ዞን በተያዘው መኸር ከ48 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በቢራ ገብስ እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በጽሕፈት ቤቱ የአዝዕርት ልማት ባለሙያ አቶ ደጀኔ ደቡሼ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ ለቢራ ገብስ ልማት ተስማሚ የሆኑ ወረዳዎች ተለይተው መሬቱን በዘር የመሸፈን ስራ በተጠናከረ ሁኔታ እየተከናወነ ይገኛል። 


 

ይህም የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ ግብዓትን በበቂ ሁኔታ ለመተካትና የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ በተያዘው መኸር በ48 ሺህ 465 ሄክታር መሬት ላይ የቢራ ገብስ እየለማ መሆኑን ገልጸው ለስኬታማነቱም በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ባለሙያዎችና አጋር አካላት በቅንጅት አርሶ አደሩን በቅርበት እያገዙ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግም የተሻሻሉ የቢራ ገብስ ዝርያዎችን እና የግብርና ግብዓትን ለአርሶ አደሮች ማቅረብን ጨምሮ፣ ማሳዎችን በኩታ ገጠም የማደራጀት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስታውሰዋል። 

በተለይም በአምቦ፣ አዳ በርጋ፣ ጅባት፣ ጀልዱ፣ ድሬ እንጪኒ፣ ኤጄሬ እና ኤጀርሳ ለፎ ወረዳዎች የቢራ ገብስ ልማት ስራው በስፋት ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች መካከል በዋናነት ተጠቃሽ መሆናቸውን አንስተዋል።

እስካሁን በተደረገው እንቅስቃሴ ከሁለት ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ታርሶና ለስልሶ በዘር የተሸፈነ ሲሆን፣ በዚህ የልማት ስራ ላይም 5 ሺህ 520 አርሶ አደሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ ብለዋል። 

በምርት ዘመኑ ከሚለማው መሬት በአጠቃላይ ከ1 ሚሊዮን 796 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝም አስታውቀዋል። 

የዘንድሮው የገብስ ልማት ስራ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ465 ሄክታር መሬት ብልጫ እንዳለውም ጠቁመዋል።


 

በዞኑ የአምቦ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ገላና ሰቦቃ በሰጡት አስተያየት፤ በዘንድሮው አዝመራ አንድ ሄክታር ማሳቸውን በቢራ ገብስ ዘር መሸፈናቸውን ተናግረዋል። 

የተሻለ ምርት ለማግኘትም ምርጥ ዘርና የምርት ማሳደጊያ ማዳበሪያ በመጠቀምና በግብርና ባለሙያ በሚሰጣቸው ምክረ ሐሳብ በመታገዝ የግብርና ስራቸውን እያከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።


 

የዚሁ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ሌላኛው አርሶ አደር ብርሃኑ ተሾመ በበኩላቸው፤ በቢራ ገብስ ልማት ሥራ ላይ መሳተፍ ከጀመሩ ሰባት ዓመታትን እንዳሳለፉ ገልጸዋል። 

በዚህ ዓመትም በግብርና ባለሙያዎች ድጋፍ ታግዘው የተሻለ ምርት ለማግኘትና ይበልጥ ተጠቃሚ ለመሆን ተግተው እየሰሩ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም