በዞኑ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በስፋት ለማምረት ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በስፋት ለማምረት ትኩረት ተሰጥቷል
አዳማ ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- በምስራቅ ሸዋ ዞን የግብርናውን ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችሉና ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በስፋት ለማምረት ትኩረት መሰጠቱን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ገለፀ።
የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ለ2018/19 ዓ.ም የምርት ዘመን ለውጭ ገበያ የሚቀርቡ የጥራጥሬና የብርዕ ሰብሎችን ለማምረት በትኩረት እየተሰራ ነው።
የግብርናውን ምርታማነት ለማሳደግም ለግብዓት አቅርቦት፣ ለግብርና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ለባለሙያ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።
ይህም የዞኑን የግብርና ምርታማነት በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባለፈ፣ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችን በስፋት ለማምረት እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።
ወደ ውጭ ከሚላኩ ምርቶች መካከልም ቦሎቄና ሽንብራን በኩታ ገጠም በማልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ልዩ ትኩረት መሰጠቱን አስረድተዋል።
ባለፈው የበጀት ዓመት 1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ኩንታል ቦሎቄ መገኘቱን የገለጹት አቶ አብነት፤ ከተመረተው ምርት ውስጥ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታሉ ለውጭ ገበያ መቅረቡን ጠቁመዋል።
በዘንድሮው የመኸር ወቅት ተግባሩን ይበልጥ በማስቀጠል፣ ከ80 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም በቦሎቄ በማልማት ከ2 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን አስታውቀዋል።
ከዚህ አኳያ ሽንብራና ሌሎች የጥራጥሬ ሰብሎችን በ12 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ በማልማት ለኢንዱስትሪ ግብዓትና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።
በተጨማሪም የጥጥ ልማትን በሙከራ ደረጃ በመተግበር ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት ለማዋል፣ እንዲሁም የአርሶ አደሩንና የአርብቶ አደሩን ገቢ ለማሳደግ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።