የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ መስተንግዶ እንድናገኝ አስችሎናል- ተገልጋዮች - ኢዜአ አማርኛ
የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ቀልጣፋ መስተንግዶ እንድናገኝ አስችሎናል- ተገልጋዮች
ወልቂጤ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ጊዜና ገንዘብ ከመቆጠብ ባለፈ ቀልጣፋ መስተንግዶ እንድናገኝ አስችሎናል ሲሉ የአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ተናገሩ።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጭነት በመላ ሀገሪቱ ተግባራዊ የተደረገው የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት በአጭር ጊዜ ውስጥ ትልቅ ስኬት የተመዘገበበት ሆኗል።
አገልግሎቱ የተበታተኑ የመንግስት አገልግሎቶችን በአንድ ማዕቀፍ እና በአንድ ማእከል ለዜጎች የዲጂታል አገልግሎት የሚሰጥበት ዘመናዊ አሰራር ሲሆን ጊዜንና ወጭን ከመቆጠብ ባለፈ ለመልካም አስተዳደር ችግር ሁነኛ መፍትሄ ሆኗል።
በአንድ ማእከል በርከት ያሉ አገለግሎቶች የሚሰጡበት የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት እየተስፋፋና በዜጎች ዘንድ በብዛት እየተለመደ መጥቷል።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተለያዩ ከተሞች ሰባት የመሶብ የአንድ ማዕከላት ተከፍተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛሉ።
በክልሉ የመሶብ አንድ ማእከል አገልግሎት ከሚሰጥባቸው ማእከላት መካከል የኢዜአ ሪፖርተር በወልቂጤ ከተማ ሲገለገሉ ያገኛቸውን ደንበኞች አነጋግሯል።
ከተገልጋዮቹ መካከል ወይዘሮ ብርዝነሽ ጋሚ እና አቶ ሃብታሙ እሸቴ፤ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ጊዜና ገንዘብ ከመቆጠብ ባለፈ ቀልጣፋ መስተንግዶ እንድናገኝ አስችሎናል ብለዋል።
በማእከሉ ዲጂታል ፋይዳ ለማውጣት እና የፖስታ አገልግሎት ሲጠቀሙ ያገኘናቸው ወይዘሮ ብርዝነሽ፣ በማእከሉ በፍጥነት እና በእንክብካቤ ጉዳያቸውን ፈፅመው መጨረሳቸውን ተናግረዋል።
ለንግድ ፈቃድ እድሳት አገልግሎት የመጡት አቶ ሃብታሙ እሸቴ በበኩላቸው፤ የመሶብ አንድ ማዕከል አገልግሎት ለህዝብ ተብሎ የተሰራ ለመልካም አስተዳደር ችግር ሁነኛ መፍትሄ ያስገኘ መሆኑን ገልጸዋል።፡
የውክልና አገልግሎት ለመስጠት መጥተው ጉዳያቸውን በፍጥነት ማጠናቀቃቸውን የተናገሩት አቶ አብዱልፈታ ስራጅ፤ አገልግሎቱ እንግልትና መጉላላትን ያስቀረ አስደናቂ አሰራር መሆኑን ገልጸዋል።
በማእከሉ የህግ ባለሙያ የሆኑት ወይዘሮ ግሩምነሽ ኤልያስ፤ በቴክኖሎጂ የተደራጀው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ከዚህ ቀደም ሁለትና ሦስት ቀናት ይፈጅ የነበረውን ጉዳይ በደቂቃዎች በማጠናቀቅ ፈጣን ምላሽ እየሰጠ ነው ብለዋል።
የወልቂጤ ከተማ የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት አስተባባሪ አቶ ሄኖክ ወልደገብርኤል በበኩላቸው፣ ማእከሉ ለማህበረሰቡ ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ገልጸዋል።
በማእከሉ አሁን ላይ የሰባት የተለያዩ ተቋማት 24 አገልግሎቶች እየተሰጡበት መሆኑን ጠቁመው በቀጣይ የመጨመር እቅድ መኖሩን ተናግረዋል።