ቀጥታ፡

በምስራቅ ጎጃም ዞን በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ ይሆናሉ

ደብረ ማርቆስ ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- በምስራቅ ጎጃም ዞን በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ የህብረተሰብ ክፍሎች ተጠቃሚ  እንደሚሆኑ የዞኑ ሴቶች ወጣቶችና ማህበራዊ ጉዳይ መምሪያ ገለፀ፡፡

የመምሪያው ኃላፊ ወይዘሮ አሞኘሽ መሀመድ ለኢዜአ እንደገለጹት፤በክረምቱ የበጎ ፈቃድ ስራ ከ 636 ሺህ በላይ ወጣቶችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ይሳተፋሉ።


 

በዚሁ ወቅት በሚካሔደው የበጎ ፈቃድ ስራም ከአንድ ቢሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የልማት ስራ እንደሚከናወንም ነው የተናገሩት።

በዚህም ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በ17 የስራ ዘርፎች የሚካሄደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱ ከ 2 ሺህ 552 ዩኒት በላይ ደም መለገስን ጨምሮ ከሶስት ሺህ በላይ የአረጋዊያንና የአቅመ ደካሞች ቤቶችን በአዲስ የመገንባትና የመጠገን ስራ እንደሚከናወን አስረድተዋል።

በዚሁ ወቅት ከ260 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን በመትከል፣ በአካባቢ ፅዳትና ውበት ጥበቃ፣ በትምህርትና ሌሎች ተግባራት በጎ ፈቃደኞችን በማሰማራት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።


 

‎በዞኑ የአንደድ ወረዳ የአንበር ከተማ ነዋሪ ወጣት ደግሰው ደሴ፤  ባለፉት ዓመታት በክረምትና የበጋ በጎ ፈቃድ አገልግሎት በመሰማራት ህብረተሰቡን እያገለገለ መሆኑን ተናግሯል።

በአሁኑ ወቅትም በተለያዩ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠሉን ነው የሚናገረው።

የጎዛምን ወረዳ የጥጃን ቀበሌ ነዋሪ አቶ መልስ ገናነው በበኩላቸው፤ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የአቅመ ደካሞችን እርሻ በመዝራት፣ በማረምና የመንከባከብ ስራ ላይ መሰማራታቸውን ተናግረዋል።

በዞኑ ባለፈው ዓመት በክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰጭዎች ለተለያዩ ተግባራት ይወጣ የነበረ ከ900 ሚሊዮን ብር በላይ የመንግስት ገንዘብ ማዳን መቻሉም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም