ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢንቨስትመንት የቁልፍ መሰረተ ልማት ተቋማትን ደኅንነት መጠበቅ የሚያስችል አቅም ፈጥሯል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የዲጂታል መሰረተ ልማት ኢንቨስትመንት የዜጎችንና የቁልፍ መሰረተ ልማት ተቋማትን ደኅንነት መጠበቅ የሚያስችል አቅም መፍጠሩን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ ገለጹ።

ዓለም አቀፉ የፓርላማ የመረጃ ደኅንነት ፎረም ከዛሬ ሐምሌ 3 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ስብሰባውን በአዲስ አበባ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መሰብሰቢያ አዳራሽ ማካሄድ ጀምሯል።


 

በመድረኩ የሰው ሰራሽ አስተውሎት አጠቃቀም፣ የሳይበር ደኅንነት፣ ቁልፍ መሰረተ ልማቶች ጥበቃ፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና መሰል ዓለምአቀፍ አሳሳቢ ጉዳዮች ላይ በስፋት ይመከራል ተብሎ ይጠበቃል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ የደኅንነት ፈተናዎችን በአፋጣኝ ምላሽ የሚሰጥና በአጋርነት መርህ ላይ የተመሰረተ በርካታ ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነች ነው።

በዚህም ቀጣናዊ ጠንካራ የትብብር ማዕቀፎችን በመዘርጋት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርንና በሰዎች መነገድ ወንጀልን ለመከላከል እየሰራች መሆኗን ገልጸዋል።

ቀጣናዊ ሰላምና ደኅንነትን በማስጠበቅ፣ የሽብር ቡድኖችን እንቅስቃሴ ከማክሸፍ ባሻገር፣ ልማትን በማፋጠን ድኅነትንና ሥራ አጥነትን በጋራ ለመቀነስ አስደናቂ ውጤቶች እየተመዘገቡ መሆኑን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ የዲጂታል ኢንቨስትመንት የሰው ሰራሽ አስተውሎት፣ መሠረተ ልማትና ሳይበር ደኅንነት አቅምን በማጎልበት፣ የዜጎችንና ቁልፍ ብሔራዊ ተቋማትን ለመጠበቅ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ ያካሄደችው ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫም አካታች፣ ነፃና ፍትሐዊ እንዲሁም ለሕገ-መንግሥታዊ አስተዳደርና ለሕግ የበላይነት ያላትን ቁርጠኝነት ያሳየ መሆኑን ገልጸዋል።

በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው፤ በአሁኑ ወቅት ዓለም እያጋጠሟት ያሉ ስጋቶች ውስብስብና በፍጥነት የሚቀያየሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።


 

መንግሥታትም የሳይበር ወንጀሎችን ለመከላከል የመረጃ ልውውጥና ሕጋዊ ማዕቀፎችን በማጣጣም ትብብራቸውን ማሳደግ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያና አሜሪካ የጤና ዘርፍ አጋርነት ውጤታማ ተግባራትን እያከናወኑ ነው ያሉት አምባሳደሩ፤ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመከላከልም በትብብር እየተሰራ ነው ብለዋል።

በፎረሙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ታገሰ ጫፎ፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት ዋና ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ የፓርላማ መረጃና ደህንነት ፎረም መስራች ሮበርት ፒቴንገር፣ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቬን ማሲንጋን ጨምሮ የተለያዩ ሀገራት የፓርላማ አባላት እየተሳተፉ ይገኛሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም