ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለጫናዎች ያልተበገረ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ አከናውናለች- ምሁራን - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ለጫናዎች ያልተበገረ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ አከናውናለች- ምሁራን
ጅማ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ለጫናዎች ያልተበገረ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወኗን የጅማና የመቱ ዩኒቨርሲቲዎች ምሁራን ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የውጭ ግንኙነትን በተመለከተ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ ውስብስብ፣ አሻሚና ኢ-ተገማች በሆነ ዓለም ዲፕሎሚያዊ አካሄድ ፕራግማቲክ (ተለዋዋጭ) ሊሆን እንደሚገባ ማንሳታቸው ይታወሳል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም አካሄዱ 3ቱ መ'ዎችን ማለትም መቋቋም፣ መጠቀም መግራት የሚባሉትን ተግባራዊ በማድረግ የዓለምን ተለዋዋጭ ባህሪ በመቋቋም የኢትዮጵያን የውሳኔ ሉዓላዊነት ማስጠበቅ መሆኑን አመልክተዋል።
ይህንኑ በማስመልከት ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ ምሁራን እንደገለፁት፤ ኢትዮጵያ ለየትኛውም አካል ያልወገነ፣ ሚዛናዊ እና ጥንቃቄ የተሞላበት ዲፕሎማሲ መከተሏ ባለፉት አምስት ዓመታት ስኬቶችን እንድታስመዘግብ አድርጓታል።
ኢትዮጵያ ባለፉት አምስት ዓመታት ለጫናዎች ያልተበገረ ስኬታማ የዲፕሎማሲ ስራ ማከናወኗንም ገልጸዋል።
በመቱ ዩኒቨርሲቲ የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህር ተገኝ ደምሴ፤ ያለፉት ዓመታት የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ጉዞ ቀላልና አልጋ በአልጋ እንዳልነበር ይናገራሉ።
በተለይም ሀገሪቱ ከታሪካዊ ጠላቶቿ የሚሰነዘሩባትን ሴራዎች ጨምሮ በርካታ ጫናዎችን ብታስተናግድም፣ በሳል የሆነ የውሃ ዲፕሎማሲ ሥራ በመሥራት እንደ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ማሳካት መቻሏን ገልጸዋል።
የዲፕሎማሲ ስራ ለአንድ ሀገር የእድገት ጉዞ እጅግ ወሳኝ በመሆኑ ዓለም አቀፍ ህጎችን ባከበረ መልኩ መንግስት የተከተለው የዲፕሎማሲ አቅጣጫ የውስጥ እና የውጭ ጫናዎችን በመቋቋም የሚፈለገው ስኬት እንዲመዘገብ አድርጓል ብለዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ በራሷ ጥረትና ሀብት "ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ" በሚል መርህ በገጠሟት ፈተናዎች ጸንታ በመቆየት የግድብ ግንባታውን ማጠናቀቋ በቀጣናው ያላትን ተሰሚነት ማሳደግ መቻሉን አመልክተዋል።
በሀገር ውስጥም ሆነ በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በያሉበት የሀገራቸው ዲፕሎማት ሆነው ኢትዮጵያ እንደ ባሕር በር ያሉ አስፈላጊ መብቷን በሴራ ማጣቷን በማስረዳት ምላሽ እስኪያገኝ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
በጅማ ዩኒቨርሲቲ የህግ እና አስተዳደር ትምህርት ክፍል መምህር ደሊል አህመድ በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት ኢትዮጵያ ትልልቅ ዓለም አቀፍ ኩነቶችን ማስተናገዷና እንደ ብሪክስ ያሉ ስብስቦችን መቀላቀሏ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የተገኘ ትልቅ ስኬት መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ሕግን ባከበረ መልኩ ፍትሐዊ አካሄድን መከተሏ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ማጠናቀቅ የመሰሉ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችን ልታስመዘግብ መቻሏን ጠቅሰዋል።
በኢኮኖሚው ዘርፍ የተከናወኑ ተግባራት፣ የጸጥታና የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ በአንድም በሌላም መልኩ ለዲፕሎማሲው መጽናት ጠንካራ መሠረት እየሆኑ መምጣታቸውንም ምሁሩ አክለዋል።
ኢትዮጵያ 7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ዓለም አቀፍ ታዛቢ ተቋማት በተገኙበት ማካሄዷ የዚሁ የዲፕሎማሲ ስኬት አንዱ መገለጫ ነው ብለዋል።
የባሕር በር ጉዳይ ኢትዮጵያ በታሪክም በሕግም የሚገባት ፍትሐዊ መብት መሆኑን ያብራሩት ምሁሩ፤ ይህንን ለማሳካት ሁለንተናዊ ጥረቶች ተጠናክረው መቀጠል አለባቸው ብለዋል።
ባለፉት አምስት ዓመታት የተመዘገቡ ዲፕሎማሲያዊ ስኬቶችን በማስቀጠል፣ ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን ሁላችንም በጋራ ልንሰራ ይገባል ሲሉም ምሁራኑ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።