በደም እጦት ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ እናቶችና ዜጎችን ለመታደግ የበጎ ፈቃድ ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን - ኢዜአ አማርኛ
በደም እጦት ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ እናቶችና ዜጎችን ለመታደግ የበጎ ፈቃድ ስራችንን አጠናክረን እንቀጥላለን
ደብረ ብርሃን፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- በደም እጦት ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ እናቶችና ዜጎችን ለመታደግ የደም ልገሳ ተግባርን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ በደብረ በብርሃን ከተማ የሚገኙ በጎ ፈቃደኞች ገለጹ።
በሰሜን ሸዋ ዞንና በደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ10 ሺህ ዩኒት በላይ ደም በመሰብሰብ ጥቅም ላይ እንዲውል ማድረጉን የደብረ ብርሃን ደም ባንክ አገልግሎት አስታውቋል።
ከበጎ ፈቃደኛ ደም ለጋሾች መካከል ወይዘሮ ሐይማኖት ተክሌ፤ ለአራተኛ ጊዜ ደም በመለገስ የእናቶችና ህፃናትን ህይወት ለመታደግ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
በተለይም በወሊድ ወቅት በደም እጥረት ምክንያት ህይወታቸውን የሚያጡ እናቶችን ለመታደግም የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎችን በማስተባበር ደም እንዲለግሱ እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።
ሌላው ደም ለጋሽ ወጣት አበባው በላይ በበኩሉ፤ በሚተካ ደም የማይተካ ህይወትን ማትረፍ ከሚሰጠው የመንፈስና የህሊና እርካታ በላይ የሚያስደስት የበጎ ፈቃድ ስራ የለም ሲል ነው የገለጸው።
በቅርቡም ለ7ኛ ጊዜ ደም መለገሱን ጠቁሞ ከራሱ ባሻገር በህክምና ተቋማት የደም እጥረት እንዳያጋጥም በደም ልገሳ የበጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ እንደሚሳተፍ አስታውቋል።
የደብረ ብርሃን ደም ባንክ አገልግሎት ስራ አስኪያጅ አቶ በዛብህ አባይነህ ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጎ ፈቃደኞችን በማስተባበር ከ10 ሺህ ዩኒት በላይ ደም በመሰብሰብ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉን ተናግረዋል።
በአዲሱ የ2019 በጀት ዓመትም 10 ሺህ 500 ዩኒት ደም ከለጋሾች በመሰብሰብ ለ20 ጤና ተቋማት ለማቅረብ ጥረት እንደሚደረግ አስገንዝበዋል።
የደም ልገሳ እቅዱን ስኬታማ ለማድረግም ከወጣቶች በተጨማሪ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌላው ማህበረሰብ በንቃት እንዲሳተፍም ጥሪ አቅርበዋል።