ሀገራዊ ምክክሩ ለጠንካራ የሀገር ግንባታ እና ለዘላቂ አንድነት መሰረት እየጣለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሀገራዊ ምክክሩ ለጠንካራ የሀገር ግንባታ እና ለዘላቂ አንድነት መሰረት እየጣለ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ለጠንካራ የሀገር ግንባታ እና ለዘላቂ አንድነት መሰረት እየጣለ መሆኑን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዝዳንቶችና የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
በኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሞ ባለፉት ዓመታት በአጀንዳ ማሰባሰብ እና በተሳታፊዎች ልየታ ላይ ሰፊ ሥራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።
ኮሚሽኑ ከመጪው ሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ ለሚያካሂደው ዋናው ሀገራዊ ጉባኤም ስምንት ዐበይት አጀንዳዎችን ለሕዝብ ይፋ አድርጓል።
የሀገር ግንባታ፣ የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዓት፣ የፖለቲካ ውክልና እና የምርጫ ሥርዓት፣ የፌዴራል ከተሞች አዲስ አበባና ድሬዳዋ ጉዳይ፣ እንዲሁም የሃይማኖት ጉዳዮች ከአጀንዳዎቹ መካከል ናቸው።
የተቋማት ግንባታ፣ የሕግ የበላይነትና ሰብዓዊ መብቶች፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እንዲሁም የአርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ጉዳዮች፣ ሙስናና መልካም አስተዳደር እንዲሁም የሰላም ግንባታ ጉዳዮችም በዋናው ጉባኤ ምክክር የሚደረግባቸው አጀንዳዎች ናቸው።
የፌዴራል ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ይታሰብ ስዩም፤ ኢትዮጵያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ የሀገረ-መንግሥት ግንባታ ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗን አንስተዋል።
ሆኖም በታሪክ ሂደት ላይ ያጋጠሙ የፖለቲካ፣ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ቅራኔዎች ለተለያዩ ግጭቶችና አለመግባባቶች መንስኤ ሆነው ቆይተዋል ብለዋል።
ኢትዮጵያውያን ለዘመናት አብረው የኖሩ፣ በችግር ጊዜ የሚደጋገፉና በመካከላቸው ያለው ማኅበራዊ ትስስር እጅግ የጠበቀ ሕዝቦች ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።
ይህንን ጠንካራ የእርስ በርስ ትስስር እና የዳበረ የባህል እሴት በመጠቀም፣ ማንኛውንም ችግሮች በጠረጴዛ ዙሪያ በመወያየት መፍታት እንደሚቻል ገልጸዋል።
ለዚህም የተጀመረው የምክክር ሂደት ሀገራዊ መግባባትንና ዘላቂ ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ የሚያበረክት መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሰመራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት መሐመድ ኡስማን (ዶ/ር)፤ በኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁና ውይይት እንዲሁም ምክክር የሚፈልጉ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል።
ልዩነቶችን በሐሳብ የበላይነትና በጋራ መግባባት ማስተናገድ መቻሉ ለሀገር አንድነትና ሉዓላዊነት ያለው ፋይዳ እጅግ የጎላ ነው ብለዋል።
ይህ የሀገራዊ ምክክር ሂደት የሀገር ግንባታ ሂደት ዘላቂነት እንዲኖረውና ጤናማ የትውልድ ቅብብሎሽ እንዲኖር ለማድረግ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል።
በመሆኑም አሁን የሚደረጉ ምክክሮች የትውልድ ቅብብሎሹ ስኬታማ እንዲሆንና መጪው ትውልድ የውይይትና የሰላም ባህልን እንዲያጎለብት አስተዋጽኦ ይኖረዋል ነው ያሉት።
የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት አስማማው ዘገየ (ዶ/ር) ፤ ሀገራዊ ምክክሩ ለሀገር አንድነትና ለጠንካራ የሀገር ግንባታ መሠረት እየጣለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ምክክሩ አሁን ያሉ ችግሮችን ከመፍታት ባለፈ ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋችና የበለጸገች ሀገርን ለማስረከብ ያስችላል ብለዋል።
የትምህርት ተቋማት በምክክሩ ሂደት ንቁ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልጸው፣ ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አክለዋል።