ቀጥታ፡

የምክክር ኮሚሽኑ የለያቸው አጀንዳዎች ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት የሚጥሉ ናቸው

ደሴ ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):-የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን የለያቸው ስምንቱ የምክክር አጀንዳዎች ለዘላቂ ሰላምና ጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረት የሚጥሉ ናቸው ሲሉ ምሁራን ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፤ ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ሃሳብ ለማካተት ጥረት የተደረገበት መሆኑን አንስተው እድሉን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።

በወሎ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ተባባሪ ፕሮፌሰር ቴዎድሮስ ካሴ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የምክክር ኮሚሽኑ የለያቸው የምክክር አጀንዳዎች ስር የሰደዱ ችግሮችን በመለየት መፍትሔ ለመስጠት የሚያስችሉ ናቸው። 

ኮሚሽኑ ለዘመናት የዘለቁ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በምክክር በመፍታት፣ ለዘላቂ ሰላምና ለህብረ-ብሔራዊ አንድነት መጎልበት ወሳኝ ሚና እየተጫወተ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ለረጅም ጊዜ ሲንከባለሉ የቆዩ ልዩነቶችን በሰለጠነ አግባብ በመፍታት ለኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ዕድገትና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ መሠረትን የሚጥል መሆኑን ተናግረዋል። 

የምክክሩ ሂደት አሳታፊ ከመሆኑም በላይ የተለዩት የምክክር አጀንዳዎችም ችግሮችን የሚፈቱና ሰላምን ለማምጣት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል። 

በምክክር የማይፈታ ችግር የለም ያሉት ምሁሩ፤ ሁሉም በየደረጃው ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የምክክሩን ቀሪ ሂደት ውጤታማ ማድረግ፣ የጋራ ትርክት ለመገንባትና ሀገርን ለመታደግ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የታሪክ መምህርና ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር ጋሻው መሐመድ በበኩላቸው፤ የምክክር ሂደቱ ዘላቂ መፍትሔ ማምጣት የሚያስችል መሆኑን እስካሁን ከመጣበት ሂደት መረዳት ተችሏል ብለዋል። 

መገፋፋትን፣ የፖለቲካ መጠላለፍንና መገለልን በማስቀረት ችግሮችን በውይይት መፍታት እንደሚቻል ለትውልድም ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።

የተለዩት የምክክር አጀንዳዎችም ወቅታዊና ለችግሮች መፍትሔ ለመፈለግ የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል። 

አጀንዳዎቹ ለሀገረ መንግሥት ግንባታ፣ ለአደረጃጀትና ቅርጽ፣ ለሰላም ግንባታና ሌሎች ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የሚያስችሉ መሆናቸውን አስገንዝበዋል። 

የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው የምክክር ጉባኤ ስምንት ዋና ዋና የምክክር አጀንዳዎችን ይፋ ማድረጉ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም