ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ከሁለት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት የመቀንጨር ምጣኔ ተጨባጭ በሆነ መልኩ ቀንሷል

ባህር ዳር ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- በአማራ ክልል መቀንጨርን ለመከላከል በተደረገ መጠነ ሰፊ ርብርብ ከሁለት ዓመት በታች ባሉ ህጻናት ላይ ያጋጥም የነበረው የመቀንጨር ሁኔታ በተጨባጭ መልኩ መቀነሱን በክልሉ የሰቆጣ ቃል-ኪዳን ፕሮግራም ማስተባበሪያ አመለከተ።

በስርዓተ ምግብ አጠቃቀም፣ አመራረትና የአመጋገብ ባህል ላይ የሚዲያ ባለሙያዎችን ያሳተፈ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ በባህር ዳር ከተማ ተካሄዷል።

በክልሉ የሰቆጣ ቃል ኪዳን ፕሮግራም ማስተባበሪያ የማህበረሰብ ባህሪ ለውጥ ተግባቦት አማካሪ አቶ ጋሻው አዳነ እንደገለጹት፤ ፕሮግራሙ በተከዜ ተፋሰስ በሚገኙ ዞኖችና ወረዳዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ይገኛል። 

በተፋሰሱ በሚገኙ 27 ወረዳዎች ተጀምሮ የነበረውን የስርዓተ ምግብ ማሻሻል ትግበራ አሁን ላይ ወደ 133 ወረዳዎች በማስፋት ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኝም አስረድተዋል።

በዚህም ለስርዓተ ምግብ እጥረት መንስኤ የሆኑት የምግብ ግብዓት አቅርቦት ችግር፣ የአመራረት፣ የአጠቃቀምና የግንዛቤ ክፍተቶችን ለመፍታት በትኩረት መሰራቱን ገልጸዋል።

እንዲሁም የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው አትክልትና ፍራፍሬ፣ እንቁላል ጣይ ዶሮዎችንና እንስሳትን ለነፍሰ ጡርና ለሚያጠቡ እናቶች በመስጠት የተከናወነው ስራ ውጤት ማስገኘቱን አብራርተዋል።

ከአመራረት ጀምሮ አሰባጥሮ እስከ መመገብ ያለውን ችግር ለመቅረፍ በተሰራው ስራ፣ ቀደም ሲል 53 በመቶ ደርሶ የነበረውን ከሁለት ዓመት በታች የህጻናት መቀንጨር ምጣኔ አሁን ላይ ወደ 27 በመቶ ዝቅ ማድረግ ተችሏል ብለዋል። 

ይህም ጤንነቱ የተጠበቀ፣ አእምሮው የዳበረና አምራች ትውልድ በመፍጠር የነገ ሀገር ተረካቢ ዜጋን ከመሰረቱ የመገንባት ስራው ስኬት እያስመዘገበ ለመሆኑ ትልቅ ማሳያ መሆኑን አስረድተዋል።

በተለይም አንዲት እናት ነፍሰ ጡር ከሆነችበት ዕለት አንስቶ ባሉት ወሳኝ አንድ ሺህ ቀናት ውስጥ የእርሷንና የህጻኑን አመጋገብ በማሻሻል ችግሩን መቅረፍ እንደሚቻል በተከናወኑ ተግባራት ማረጋገጥ መቻሉን ገልጸዋል። 

የሚዲያ ባለሙያዎችም ቃል ኪዳኑ እያከናወነ ያለውን ተግባር በአግባቡ በመረዳት፣ በተገኙ ለውጦችና ተሞክሮዎች ላይ በማተኮር ለህብረተሰቡ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የድርሻቸውን እንዲወጡም አሳስበዋል።


 

የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ አባይ መንግስቴ በበኩላቸው፤ በክልሉ የሚታየው የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ችግር የምርት ማነስ ሳይሆን የግንዛቤ ክፍተት ውጤት መሆኑን ገልጸዋል። 

ይህን ችግር በመሰረታዊነት ለመቀየርም መንግስት የቃልኪዳን ስምምነቱን ወደ ስራ በማስገባት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን በማከናወን ለውጥ እንዲመጣ ማስቻሉን ኃላፊው አስረድተዋል። 

የሚዲያ ተቋማትና ባለሙያዎችም እየተሰራ ያለውን ስራ በዘገባዎቻቸው ተንትነው በማስረዳት፣ ችግሩን ሙሉ በሙሉ በመቅረፍ ጤናማ ትውልድ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ማገዝ እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

ለቃል ኪዳኑ ተግባር ማስፈጸሚያም በራሱ በፕሮግራሙ፣ እንዲሁም በፌደራልና በክልል መንግስታት አማካኝነት በየዓመቱ ከ1 ነጥብ 13 ቢሊዮን ብር በላይ እየተመደበ መሆኑም ተመላክቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም