የተፈጠረው አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ሥርዓት በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጠረው አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ሥርዓት በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ዕድል ፈጥሯል
ወልቂጤ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- በኢትዮጵያ የተፈጠረው አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ስርዓት በሃገር ሰላምና ልማት ላይ በትብብር ለመስራት የሚያስችል እድል መፍጠሩን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 30ኛ መደበኛ ጉባኤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ባሳለፍነው ማክሰኞ ዕለት መካሄዱ ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዲሞክራሲ ግንባታና የፖለቲካ ተሳትፎን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በወቅቱም፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብልጽግና ፓርቲ 85 በመቶ መቀመጫ ላይ ብቻ በመወዳደር ቀሪውን ለተፎካካሪ ፓርቲዎች በመተው፣ የዲሞክራሲ ቀናዒነት የታየበት ምርጫ ማካሄዱን ገልጸዋል።
በጉዳዩ ላይ ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ በሀገሪቱ የተፈጠረው አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ሥርዓት በሀገር ሰላምና ልማት ላይ በትብብር ለመሥራት የሚያስችል ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
የክልሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢዜማ ፓርቲ ተወካይ አቶ ደምስ ገብሬ እንዳሉት፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ የመረጠበትና በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት ነው።
ፓርቲያቸው ኢዜማም በምርጫው በመሳተፍ ለክልልና ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎችን ማግኘቱን ጠቅሰው፤ ባለፉት ዓመታትም በብልጽግና መንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የነበረውን ሚና በተገቢው መንገድ መወጣቱን ገልጸዋል።
መንግሥት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቶችን አቅም በማዳበር የአጋዥነት ሚና እንዲኖራቸው ማድረጉ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ደምስ፤ በቀጣይም በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይ ሊተገበሩ በታሰቡ ጉዳዮች ዙሪያ የሰጡት ዝርዝር ማብራሪያ አሳታፊና አካታች የፖለቲካ ሥርዓት ለመዘርጋቱ አመላካች መሆኑን ያነሱት ደግሞ የጉራጌ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባልና የጎጎት ፓርቲ ተወካይ አብዱላዚዝ ሙሰማ (ዶ/ር) ናቸው።
ሀገር የሚገነባው በሁሉም ኢትዮጵያውያን አስተዋፅኦና ርብርብ በመሆኑ፤ የፖለቲካ ፓርቲዎች ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ በትብብርና በጤናማ ፉክክር መሥራት ይገባናል ብለዋል።
የጉራጌ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢና የዞኑ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ናሰር ሐሰን በበኩላቸው፤ የለውጡ መንግሥት የዲሞክራሲ ሥርዓትን ለማጎልበት ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ በሰጡት ማብራሪያ፤ የአገልግሎት ዘመናቸውን ካጠናቀቁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አባላት ጋር አብሮ ለመሥራት ያሳዩት ፍላጎት አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ሥርዓት ለመኖሩ ማረጋገጫ ነው ሲሉም አመልክተዋል።