ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክህሎትና በስነ- ምግባር የታነጹ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል - ኢዜአ አማርኛ
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በክህሎትና በስነ- ምግባር የታነጹ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል
ጋምቤላ ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):-ባለፉት የለውጥ ዓመታት በትምህርት ጥራት ላይ በተከናወኑ ተግባራት፣ በክህሎትና በሥነ-ምግባር የታነጹ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የ2018 በጀት ዓመትን አስመልክተው በሰጡት ማብራሪያ፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
በተለይም ከቅድመ-መደበኛ ጀምሮ በሁሉም የትምህርት ደረጃዎች በርካታ የፖሊሲና የሪፎርም ሥራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዘርፉ ተጨባጭ ውጤቶች መመዝገባቸውን አብራርተዋል።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንም ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ባለፉት የለውጥ ዓመታት በየደረጃው የሚሰጡ የሥልጠና መመዘኛዎችን ጨምሮ በተከናወኑት የሪፎርም ሥራዎች በትምህርት ጥራት ላይ ተጨባጭ ለውጥ እየተመዘገበ መሆኑን ገልጸዋል።
በዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሽብሩ ዘሪሁን (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በትምህርት ዘርፉ የተከናወኑ የለውጥ ሥራዎች በተለይም በትምህርት ጥራት ላይ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ አስችለዋል።
የሪፎርም ሥራዎችን ጨምሮ የቅድመ-ምረቃ መውጫ፣ የድኅረ-ምረቃ መግቢያና የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናዎች በዩኒቨርሲቲዎች መሰጠታቸው በትምህርት ጥራት ላይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል።
ባለፉት የለውጥ ዓመታት በተከናወኑት የለውጥና የሪፎርም ስራዎች በክህሎት፣ በዕውቀትና በስነ-ምግባር የታነጹ ዜጎችን በማፍራት ረገድ ውጤታማ ተግባራት እንዲከናወኑ አስችለዋል ብለዋል።
የጋምቤላ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ፣ የምርምር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት አማካሪ ተባባሪ ፕሮፌሰር ጀምበሩ ዓለሙ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገር በዘርፉ በተከናወኑት የስልጠናና ለውጥ ስራዎች በትምህርት ጥራት በርካታ ስኬቶች ተገኝተዋል ብለዋል።
በተለይም የዩኒቨርሲቲ የመውጫ ፈተናን ጨምሮ በአጠቃላይ በየደረጃው የሚሰጡት የክልልና ሀገር አቀፍ መመዘኛዎች ለትምህርት ጥራት የጎላ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን ተናግረዋል።
ቀደም ሲል ወደ ዩኒቨርሲቲው ይገቡ የነበሩ ተማሪዎች ከፍተኛ የአቅም ችግር እንደነበረባቸው ያስታወሱት ተባበሪ ፕሮፌሰሩ፤ አሁን ላይ ጠያቂና ተመራማሪ ተማሪዎች እየመጡ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ቀደም ሲል የዩኒቨርሲቲ መውጫ ፈተና ሲጀመር የተማሪዎች መጠነ ማለፍ 25 ከመቶ ብቻ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ወደ 91 ነጥብ 2 ከመቶ ከፍ ማለቱን ተባባሪ ፕሮፌሰሩ በማሳያነት ጠቅሰዋል።