የአውሮፓ ኃያላን ፍጥጫ፤ የስፔንና የቤልጂየም ተጠባቂ የዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ - ኢዜአ አማርኛ
የአውሮፓ ኃያላን ፍጥጫ፤ የስፔንና የቤልጂየም ተጠባቂ የዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 3/ 2018 (ኢዜአ):- 23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር ስፔን ከቤልጂየም ዛሬ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ።
ጨዋታው ምሽት አራት ሰዓት ላይ በሎስ አንጀለስ ስታዲየም ይካሄዳል።
ስፔን በ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ፖርቹጋልን 1 ለ 0 አሸንፋለች።
የአንድ ጊዜ የውድድሩ አሸናፊ ስፔን በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኳ ለሰባተኛ ጊዜ ለሩብ ፍጻሜ አልፋለች።
ተጋጣሚዋ ቤልጂየም ከአዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችውን አሜሪካን 4 ለ 1 በመርታት ለአራተኛ ጊዜ ወደ ሩብ ፍጻሜ መግባት ችላለች።
ሁለት ሀገራት በዓለም ዋንጫው ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።
ሜክሲኮ እ.አ.አ በ1986 ባዘጋጀችው 13ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በሩብ ፍጻሜው ተገናኝተው ቤልጂየም በመለያ ምት 5 ለ 4 በማሸነፍ ለግማሽ ፍጻሜ አልፋለች።
እ.አ.አ በ1990 በጣልያን በተካሄደው 14ኛው የፊፋ የዓለም ዋንጫ በምድብ አምስት ተገናኝተው ስፔን ቤልጂየምን 2 ለ 1 አሸንፋለች።
ሁለቱ ሀገራት ከ36 ዓመታት በኋላ በዓለም ዋንጫው መድረክ ተገናኝተዋል።
ሀገራቱ በውድድሮች እና በወዳጅነት ጨዋታዎች 23 ጊዜ ተገናኝተው ስፔን 12 ጊዜ ድል ሲቀናት ቤልጂየም በአምስት ጨዋታዎች አሸንፋለች። በቀሪ ስድስት ጨዋታዎች አቻ ተለያይተዋል።
ስፔን በ23ቱ ጨዋታዎች ላይ 46 ጎሎችን ከመረብ ላይ ስታሳርፍ ቤልጂየም 22 ግቦችን አስቆጥራለች።
የ29 ዓመቱ አጥቂ ሚኬል ኦያርዛባል ሁለት ግቦችን በማስቆጠር የስፔን የውድድሩ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ነው።
የ33 ዓመቱ የፊት መስመር ተሰላፊ ሮሜሎ ሉካኩ ለቤልጂየም በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ሶስት ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ሊያንድሮ ትሮሳርድ እና ቻርልስ ደ ኬቴላሬ በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን አስቆጥረዋል።
በፊፋ የዓለም ሀገራት የእግር ኳስ ደረጃ ስፔን 3ኛ፣ ቤልጂየም ደግሞ 8ኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ።
ላሚን ያማል እና ሮድሪ ከስፔን፣ ኬቨን ደ ብሮይን እና ሮሜሎ ሉካኩ ከቤልጂየም በጨዋታው ልዩነት ይፈጥራሉ ተብለው የሚጠበቁ ናቸው።
ሁለቱ የአውሮፓ ኃያላን ሀገራት በዛሬው ጨዋታ አዝናኝ እና ማጥቃት ላይ የተመሰረተ የጨዋታ እንቅሰቃሴ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዛሬው ጨዋታ አሸናፊ በግማሽ ፍጻሜው ከፈረንሳይ ጋር ይጫወታል።
ፈረንሳይ ትናንት ሞሮኮን 2 ለ 0 በማሸነፍ ግማሽ ፍጻሜውን ተቀላቅላለች።