ፈረንሳይ ሞሮኮን በመርታት ለግማሽ ፍጻሜ አለፈች - ኢዜአ አማርኛ
ፈረንሳይ ሞሮኮን በመርታት ለግማሽ ፍጻሜ አለፈች
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2018 (ኢዜአ)፦ በ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ የሩብ ፍጻሜ ማለፍ መርሐ ግብር ፈረንሳይ ሞሮኮን 2 0 አሸንፋለች።
ማምሻውን በቦስተን ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ኪሊያን ምባፔ በ60ኛው እና ኡስማን ዴምቤሌ በ65ኛው ደቂቃ ግቦቹን አስቆጥረዋል።
ምባፔ በ28ኛው ደቂቃ ፍጹም ቅጣት ምት ስቷል።
ፈረንሳይ በጨዋታው ፍጹም ብልጫ ወስዳለች።
የተደራጀ መከላከል እና የመልሶ ማጥቃት የአጨዋወት ስልት የተከተለችው ሞሮኮ ግልጽ የግብ እድሎችን መፍጠር ተስኗታል።
የ27 ዓመቱ ኪሊያን ምባፔ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ ያስቆጠራቸውን ጎሎች ብዛት ስምንት በማድረስ ከአርጀንቲናው ሊዮኔል ሜሲ ጋር በጎል እኩል በመሆን ሶስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ብልጫ ወስዶ የከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነቱን እየመራ ይገኛል።
በአጠቃላይ በውድድሩ ላይ 20 ጎሎች ከመረብ ላይ በማሳረፍ በምንጊዜም ከፍተኛ አስቆጣሪነቱ ከሜሲ (21 ጎል) በአንድ አንሶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል።
ምባፔ በዓለም ዋንጫው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ 12ኛ ጎሉን በማስቆጠር በውድድሩ አዲስ ክብረ ወሰን አስመዝግቧል።
ለብሔራዊ ቡድኑ 64ኛ ጎሉን ከመረብ ላይ አሳርፏል።
ምባፔ በ77ኛው ደቂቃ ጉዳት አጋጥሞት ተቀይሮ ወጥቷል።
የባለንዶር ባለቤቱ ኡስማን ዴምቤሌ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አምስተኛ ጎሉን አስቆጥሯል።
ውጤቱን ተከትሎ ፈረንሳይ ግማሽ ፍጻሜውን የተቀላቀለች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች። በዓለም ዋንጫው ለግማሽ ፍጻሜ ስታልፍ የአሁኑ ለሰባተኛ ጊዜ ነው።
ፈረንሳይ በግማሽ ፍጻሜው ከስፔን እና ቤልጂየም አሸናፊ ጋር ትጫወታለች።
ሞሮኮ የዓለም ዋንጫ ጉዟዋ ሩብ ፍጻሜው ላይ አብቅቷል። ለተከታታይ ዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ የመግባት ህልሟ ሳይሳካ ቀርቷል።
በሩብ ፍጻሜው ላይ አፍሪካን የወከለችው ብቸኛ ሀገር ሞሮኮ ከውድድሩ ተሰናብታለች።
የሰሜን አፍሪካዋ ሀገር ከተሳተፉ 10 ቡድኖች መካከል የተሻለ ርቀት መጓዝ ችላለች።
ሞሮኮ በ22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ የደረሰች የመጀመሪያዋ የአፍሪካ ሀገር መሆኗ የሚታወስ ነው።
በዘንድሮ የዓለም ዋንጫ አፍሪካ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ 10 ሀገራት አሳትፋለች።