መንግሥት የሰላም በሩን ክፍት ማድረጉ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ካለው ቁርጠኛ አቋም የሚመነጭ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት የሰላም በሩን ክፍት ማድረጉ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ካለው ቁርጠኛ አቋም የሚመነጭ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የሰላም በሩን ክፍት ማድረጉ የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ካለው ቁርጠኛ አቋም የሚመነጭ መሆኑን አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት የሥራ አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤቱ አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም መንግሥት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላም ለመገንባት ሁልጊዜም ቢሆን የሰላም በር ክፍት ማድረጉን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ የጸጥታ ኃይል ከምንጊዜውም በላይ በአስተማማኝ ቁመና ላይ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የሀገር መከላከያ ሠራዊትም በላቀ ቴክኖሎጂና በሰው ኃይል በጽኑ መሠረት መገንባቱን አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ቅንጣት ታክል ስጋት የሚሆን አንዳች ኃይል እንደሌለም ነው አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩት።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም፤ የኢትዮጵያን ሰላም፣ ልማትና ዕድገት ለማደናቀፍ የሚጥሩ የውስጥ ኃይሎች ፍላጎት ፈጽሞ አይሳካም ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ላይ ትንኮሳ የሚፈጽም አንዳች ኃይል ቢኖር እንኳን ከመንግሥት ጋር በመተባበር የሀገርን ደኅንነት ለማስከበር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪ የመዲናዋ ነዋሪዎች መካከል ገዛኸኝ ደበበ፤ ቅድመ አያቶች በከፈሉት ውድ መስዋዕትነት ትውልዱ ሉዓላዊ ነፃነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያን እንዲረከብ ማስቻሉን አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅትም ዜጎች በኢትዮጵያ ሉዓላዊ ክብር ላይ ሊቃጣ የሚችልን አንዳች ትንኮሳ ለመቀልበስ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
የታሪካዊ ጠላቶችን ተልዕኮ በመሸከም ኢትዮጵያን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ የሀገር ውስጥ ኃይሎችም፣ ውይይትና ምክክርን በማስቀደም ለሀገር ሉዓላዊ ክብር በጋራ መስራት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ፀሐይ አሰፋ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በአጭር ዓመታት ውስጥ በሁሉም ዘርፍ አስደማሚ የልማት ውጤት እያስመዘገበች እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በጫካ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችም የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበል፣ ውይይትና ምክክርን አስቀድመው ለኢትዮጵያ ዕድገት መፋጠን በትብብር መስራት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
በሁሉም ዘርፍ የሚመዘገበው የኢትዮጵያ የልማት ውጤት የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት የሚረጋገጥበትን ወሳኝ ዕድል ፈጥሯል ያሉት ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ በጸሎት ዮሐንስ ናቸው።
ኢትዮጵያውያንም ከመንግሥት ጋር በመተባበር የሀገርን ዘላቂ ሰላምና ልማት በማስቀጠል፣ ለሀገር ሉዓላዊ ደኅንነት ከመንግሥት ጋር በትብብር መስራት እንደሚኖርባቸው ገልጸዋል።
ቅድመ አያቶች በዓድዋ፤ የአሁኑ ትውልድ ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት ያደረጉት በሕብር የታተመ አንድነትም፣ ማንኛውንም የውጭ ትንኮሳና ጫና መቀልበስ እንደሚቻል ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።
ሌላኛዋ የመዲናዋ ነዋሪ ፀሐይ ተፈራ በበኩላቸው፤ መንግሥት ለዘላቂ ሰላም ግንባታ የሚሰጠው ተደጋጋሚ ዕድል የሀገር ልማትና ዕድገትን ለማስቀጠል የሚመነጭ ቁርጠኛ አቋም መሆኑን ገልጸዋል።
በቀጣይም የሀገርን ሰላምና ዕድገት ለማስቀጠል ከመንግሥት ጋር እጅ ለእጅ በመያያዝ በትብብር መስራት ይጠበቅብናል ነው ያሉት።