ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ አንድነቷ የተጠናከረና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 2/2018 (ኢዜአ)፦ሀገራዊ ምክክሩ አንድነቷ የተጠናከረና ዘላቂ ሰላም የሰፈነባት ሀገር ለመገንባት ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው ሲሉ  የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ከምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ሀገራዊ ምክክሩ ለዘመናት የተከማቹ ችግሮችን የሚፈታ በመሆኑ ዕድሉን መጠቀም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በምክክሩ ሂደት ከታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል ጀምሮ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ አጀንዳ የተለየበት መሆኑን ጠቁመው፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካ ምሳሌ የሚሆን ጠቃሚ ሒደት ነው ብለዋል።

የምክክሩ ዋና ዓላማ ባለፉት ዘመናት ለቅራኔ ምንጭ የሆኑና የተከማቹ ችግሮችን በጋራ መክሮ መልክ ማስያዝ እንደሆነ ጠቅሰው፣ አዲስ ማኅበራዊ ውል የሚፈጸምበት መሆኑንም አመልክተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያና የሀገራዊ ምክክር ሂደትን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎች፤ ምክክር የችግሮችን መንስኤና መፍትሔ በትክክል ለመለየት የሚያስችል ቀዳሚ መሣሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክሩ ወደ ወሳኝ ምዕራፍ መሸጋገሩንና ታሪካዊ የሆነው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ መካሄድ፣ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ትልቅ ፋይዳ እንዳለው አስታውቀዋል።

ይህ ወሳኝ ምዕራፍ ስኬታማ እንዲሆንም ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል በንቃትና በኃላፊነት ስሜት ሊሳተፍ እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ሰላማዊት ጌትነት እንደተናገሩት፤ ምክክር በሀገር ውስጥ ያሉ ችግሮችንና መፍትሔዎቻቸውን በግልጽ ለመለየት ያስችላል።

በኢትዮጵያ የሚካሄደው ምክክር ችግሮችን በዘላቂነት በመፍታት የተረጋጋች ሀገርን ለመገንባት ትልቅ መሠረት የሚጥል መሆኑን አንስተዋል።

ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ ያሬድ ደምሌ በበኩላቸው፤ የምክክር ሂደቱ አለመግባባቶችን በመፍታት የተረጋጋችና አንድነቷ የተጠናከረ ሀገር መገንባት ያስችላል ብለዋል፡፡

ጦርነትና ግጭት ዘላቂ መፍትሔ እንደማያመጡ መታወቅ እንዳለበት የገለጹት አቶ ያሬድ፤ ምክክሩ ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥና የተጀመሩ የልማት ሥራዎችን አጠናክሮ ለማስቀጠል ወሳኝ ሚና እንዳለው አጽንኦት ሰጥተዋል።

አቶ ኃይሌ ባህረ፤ ሃገራዊ ምክክሩ የቆዩ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ትልቅ መሣሪያ መሆኑን በመጥቀስ  በሀገሪቱ ያሉ ችግሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ ተነጋግሮ ለመፍታት የሚያስችል ምቹ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል።

ወይዘሮ ወሰንየለሽ ገብሩ በበኩላቸው፤  አስተማማኝና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን የምክክር ባህልን ማሳደግ አማራጭ የሌለው ተግባር በመሆኑ የሚደረገው ምክክር ለዘላቂ ሰላም ሆነ ልማትን ለማስቀጠል እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት ስታከናውነው የቆየችው የሀገራዊ ምክክር ሂደት አሁን ላይ የመጨረሻና ወሳኝ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።

ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ለሚካሄደው የሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የሚሳተፉ ተመካካሪዎች አዲስ አበባ በመግባት ላይ ይገኛሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም