የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚያከናውኗቸው ተግባራት የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ሊያጎለብቱ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚያከናውኗቸው ተግባራት የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ሊያጎለብቱ ይገባል
ሰመራ፤ሐምሌ 2/2018 (ኢዜአ)፦ በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በሚያከናውኗቸው ተግባራት የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ሊያጎለብቱ እንደሚገባ የክልሉ ገንዘብ ቢሮ አመለከተ።
በአፋር ክልል የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች በአፈፃፀም ሪፖርትና በቅንጅታዊ ተግባራት ዕቅድ ላይ በሰመራ ከተማ ውይይት አድርገዋል።
በወቅቱም የአፋር ክልል ገንዘብ ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ደረሳ መሐመድ እንደገለፁት፤ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የሚያከናውኗቸው ተግባራት የማህበረሰብ ተጠቃሚነትን ሊያጎለብቱ ይገባል።
ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ ድርጅቶቹ እርስ በርስ ተናበውና ተቀናጅተው ሊሰሩ እንደሚገባ አመልክተዋል።
ባለፈው በጀት ዓመት በክልሉ ድርጅቶቹ 60 ዋና ዋና ፕሮጀክቶችን ያከናወኑ መሆኑን ገልጸው ለፕሮጀክቶቹም በአጠቃላይ 6 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ወጪ መደረጉን አስረድተዋል።
ከፕሮጀክቶቹ መካከል 18ቱ በጤናና በሥነ-ምግብ ዘርፎች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።
ድርጅቶቹ በሚያከናውኗቸው የልማት ሥራዎች የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጨባጭ ፍላጎት ከማገናዘብ ባለፈ የሥራ ዕድሎችን ማመቻቸት እንደሚገባቸውም ምክትል ኃላፊው አመልክተዋል።
በክልሉ በተከናወኑ የትምህርት፣ የጤና፣ የውሃና ሌሎች ዘርፎች ድርጅቶቹ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ጉልህ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህንኑ ኅብረተሰብን ማዕከል ያደረገ ድጋፋቸውን አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባም አሳስበዋል።
የ"ፍሬንድሺፕ ሰፖርት አሶሴሽን" ፕሮግራም ማናጀር ወይዘሮ የማ ዳንኤል በበኩላቸው፤ ፕሮግራሙ በጤና፣ በውሃና በሰላም ግንባታ ዘርፎች ላይ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸው የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማላቅ በትጋት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
በክልሉ በተለያዩ ወረዳዎች በሕዝብና እንስሳት ጤና ዘርፎች እንዲሁም በውሃ ላይ በመሰማራት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ያጎለበቱ በርካታ ተግባራትን እንዳከናወኑ የገለጹት ደግሞ "ኮፕ" (COOP) በተሰኘው የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅት የአፋር ቅርንጫፍ አስተባባሪ አቶ መሐመድ ጎንፍሬ ናቸው።
በበጀት ዓመቱ ድርጅቶቹ በክልሉ በሚገኙ ስድስት ዞኖች ውስጥ በስፋት ተሰማርተው፣ ማኅበረሰብ ተኮር የሆኑ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በስኬት ማከናወናቸውም ተገልጿል።