የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያሳደገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን እያሳደገ ነው
ደብረ ብርሃን፤ ሐምሌ 2/ 2018(ኢዜአ):- የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የነዋሪዎችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ መሆኑን በአማራ ክልል የሰሜን ሸዋ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
መምሪያው "ተስፋን እንትከል" በሚል መሪ ሃሳብ የክረምቱን የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ የማስጀመሪያ መርሃ ግብር በሲያደብርና ዋዩ ወረዳ "ጋራ መየ" ተፋሰስ ዛሬ አካሂዷል።
የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ታደሰ ማሙሻ እንዳሉት ፤ በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የለሙ ተፋሰሶች አርሶ አደሩ ከእለት ፍጆታው ያለፈ ምርት ለማምረት የሚያስችለውን አቅምን ፈጥሮለታል።
በዋናነትም በመኖ ልማት፣ በእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ በንብ ማነብ ፣ በአትክልትና ፍራፍሬ ዘርፎች እንዲሰማሩ ማስቻሉን ገልጸዋል።
በክረምቱ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በዞን ደረጃ በ36 ሺህ 284 ሄክታር መሬት ላይ ከ298 ሚሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል ነው ያሉት።
በዘንድሮው ዓመት የሚተከሉት ችግኞች የዞኑን የደን ሽፋን ከፍ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።
በክረምቱ ሁለት ነጥብ አራት ሚሊዮን የፍራፍሬ ችግኞችን በመትከል የአርሶ አደሩን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መካሻ ዓለማየሁ በበኩላቸው ፤ህብረተሰቡ በየዓመቱ ችግኝ በመትከል ምርታማነትን በዘላቂነት ለማሳደግ የጀመረውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል ይገባዋል ሲሉ አሳስበዋል ።
የሚተከሉ ችግኞችም አሁን ያለውን አርሶ አደርና ወጣት ተጠቃሚ ከማድረግ ባሻገር የመጪውን ትዉልድ ታሳቢ ባደረገ መልኩ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
የሲያ ደብርና ዋዩ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ደሱ ምክረ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የሚተከሉ ችግኞች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸዉና ለአካባቢ ስነ ምህዳር ጥበቃ ከፍተኛ ፋይዳ የሚያበረክቱ ናቸው።
በወረዳው በያዝነው ክረምት ስምንት ነጥብ አራት ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል የሚያስችል የቦታ ዝግጅት ተካሂዶ ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።
የዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ዓለማየሁ ያዴቴ እንደገለጹት፤በዘንድሮው ዓመት ከዚህ በፊት ከተከሏቸው ችግኞች 30 ሺህ ብር ገቢ ማግኘታቸውን ጠቁመዋል ።
የተተከሉ ችግኞችን በመንከባከብ የጽድቀት ምጣኔያቸውን ለማሳደግ እንሰራለን ሲሉም ገልጸዋል።
በማስጀመሪያ መርሃ ግብሩ ላይም ከዞንና ከወረዳ የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።