ቀጥታ፡

መንግሥት ለአካታች የፖለቲካና የዴሞክራሲ ምህዳር መስፋት የሰጠው ትኩረት ለሀገር ዕድገት በትብብር መሥራትን የሚያጠናክር ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት ለአካታች የፖለቲካና የዴሞክራሲ ምህዳር መስፋት የሰጠው ትኩረት ለሀገር ዕድገት በትብብር መሥራትን የሚያጠናክር መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ገለፁ።

ከሀገራዊ ለውጡ ወዲህ በገዥው ፓርቲ ብልፅግና እና በተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ የመሥራትና ሚዛኑን የጠበቀ የፉክክርና የትብብር ምህዳር ተገንብቷል።

በዚህም የተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በመንግሥት መዋቅር ውስጥ ተመድበው እየሠሩ ሲሆን ይህም አካታች የፖለቲካ ጉዞን ከመክፈቱ በላይ ሀገርን በጋራ የማገልገል የትብብር አቅምን አሳድጓል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ በሰጡት ማብራሪያ፥ ብልፅግና ፓርቲ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ 85 በመቶ በሆኑ ወንበሮች ላይ ብቻ በመወዳደር፣ በቀሪው 15 በመቶ ወንበር ላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻቸውን እንዲወዳደሩ ዕድል መስጠቱን ተናግረዋል።

በምርጫው በርካታ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች መሳተፋቸውን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ መንግሥት ለአካታች የፖለቲካና የዴሞክራሲ ምህዳር ግንባታ ትኩረት መስጠቱን ገልጸዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች፥ መንግሥት ለአሳታፊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ የሚያደርገው ጥረት፤ ለሀገራዊ መግባባት፣ በጋራ ጉዳዮች ላይ በትብብር ለመሥራትና ለአካታች ፖለቲካ ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይም ጠቁመዋል።

ወይዘሮ መታሰቢያ ጠብቀው፤ 15 በመቶ ወንበሮች ላይ ሳይወዳደር ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻ ክፍት ማድረጉ ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ይሁነኝ ብሎ እየሠራ መሆኑን ያስመሰከረ ነው ብለዋል።

ሁሉንም ያሳተፈ ሥርዓት መገንባት፣ መንግሥት የጀመራቸውን የልማት ሥራዎች በትብብር ለማፋጠንና በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ተቀራርቦ ለመሥራት አቅም መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ሴቶች ወደ አመራርነት የመምጣት አጋጣሚያቸው እጅግ ውስን የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ግን በሁሉም ዘርፎች እኩል ተሳታፊ መሆን መቻላቸው ሌላው የአካታችነት መገለጫ መሆኑን ጠቁመዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ አቶ ዳዊት ይርባ በበኩላቸው፤ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ለማጠናከር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት አበረታች በመሆናቸው ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ገልጸዋል።

የመንግሥት ቁርጠኝነት በሐሳብ ልዕልና ላይ የተመሠረተ ፉክክርና ትብብርን በማስፋት ለዘላቂ ሰላምና ልማት መሠረት እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ወይዘሮ ውበት ደጉ በበኩላቸው፤ አሳታፊ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዜጎች ሐሳባቸውን በነፃነት በመግለጽ ለሀገራቸው ልማትና ዕድገት የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ዕድል እንደሚፈጥር አብራርተዋል።

አቶ ሺመልስ ከተማም መንግሥት በተባበረ መንፈስ ለመሥራትና ለአካታች የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያሳየው ቁርጠኝነት በሀገሪቱ የፖለቲካ ጉዞ ትልቅ ተስፋን የሚዘራ መሆኑን ተናግረዋል።

ይህም በእያንዳንዱ ዜጋ ዘንድ መደማመጥ፣ መግባባትና መተሳሰብን እንደሚፈጥር እምነታቸውን ገልጸዋል።

አሳታፊ የፖለቲካና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው ዘላቂ እንዲሆን የውይይት ባህል ወሳኝ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ ዶክተር ፍቅሩ ደስታ ናቸው።

መንግሥት ሁሉንም ያሳተፈ እና በውይይት ላይ የተመሠረተ አካሄድ ለመከተል ቁርጠኛ መሆኑ ዘላቂ ሰላምና መግባባትን ለመፍጠር ትልቅ አስተዋፅኦ እንዳለው አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም