ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይ ክልል ተተኪ ትውልድን ሆን ብሎ በመዋቅራዊ አሰራር እያጠፋና እያመከነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይ ክልል ተተኪ ትውልድን ሆን ብሎ በመዋቅራዊ አሰራር እያጠፋና እያመከነ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2018(ኢዜአ)፦ ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይ ክልል ተተኪ ትውልድን ሆን ብሎ በመዋቅራዊ አሰራር እያጠፋና እያመከነ መሆኑን የቀድሞዋ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤና የስምረት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ የምክር ቤት አባል ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም ገለጹ።
ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን "ፅምዶ" በሚል ስያሜ ከሻዕቢያ፣ ከሱዳንና ከሀገር ውስጥ ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ ኢትዮጵያን እያተራመሰ ለመኖር አልሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ቡድኑ የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት እያጣቀሰ ለዳግም ጦርነት ጊዜ መግዣነት በመጠቀም የትግራይ እናቶችን እያስለቀሰ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂም የትግራይ ክልል ወቅታዊ ሁኔታን አስመልክቶ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፤ የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት የጥይት ድምፅ በማጥፋት ለክልሉ ሕዝብ ተስፋ የሰጠ ሁነኛ የሰላም በር ነበር።
የፌዴራል መንግሥትም በሰላም ስምምነቱ መሠረት የወደሙ መሠረተ ልማቶችንና ተቋማትን መልሶ መገንባቱን ገልጸው፤ ይህም የክልሉ ሕዝብ የተረጋጋና ሰላማዊ ሕይወት የሚመራበትን ዕድል እንደፈጠረ አብራርተዋል።
ይህም የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በማቋቋም ጭምር ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ያላቸው ተቋማት በአፋጣኝ ወደ አገልግሎት እንዲመለሱ ማድረጉን አስታውሰዋል።
የቀድሞ የትግራይ ክልል ታጣቂዎችንም በተሃድሶ ስልጠና በማሳለፍ፣ ወደ ማኅበረሰባቸው ተቀላቅለው የተረጋጋ ሕይወት የሚመሩበት የገንዘብ ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱንም አክለዋል።
ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን ለትግራይ ሕዝብ ትልቅ እፎይታን ይዞ የመጣውን የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ለጊዜ መግዣነት እንደተጠቀመበት ተናግረዋል።
በዚህም ቡድኑ የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር በኃይልና በተደጋጋሚ በማፍረስ፣ በጨረባ ምርጫ ያደራጀውን ሕገ-ወጥ ምክር ቤት በመሰብሰብ ተቀባይነቱን ያጣ ካቢኔ ማዋቀሩን አስረድተዋል።
በአሁኑ ወቅትም ሕገ ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይ ክልል ተተኪ ትውልድን ሆን ብሎ በመዋቅራዊ አሰራር እያጠፋ መሆኑን ወይዘሮ ኬሪያ አስረድተዋል።
በተለይም ራሱን ለዳግም ጦርነት በማዘጋጀት፣ ሕፃናትን ከእናታቸው ጉያ በመንጠቅ የትግራይ እናቶችን የደም እምባ እያስለቀሰ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
ቡድኑ ከሀገር ውስጥና ከውጭ የጠላት ኃይሎች ጋር ያልተቀደሰ ጋብቻ በመፍጠር፣ የትግራይ ክልል ሕዝብን ለዳግም ጉስቁልና ለማመቻቸት ጥረት እያደረገ መሆኑን አንስተዋል።
ይህ ህገ ወጥ ቡድን በትግራይ ሕዝብ ላይ እያደረሰ የሚገኘው ከፍተኛ ሰብዓዊ በደልም በተለያዩ ሀገራትና በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር እየተወገዘ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ቡድኑ "ፅምዶ" በሚል ስያሜ ከሻዕቢያ፣ ከሱዳንና ከሀገር ውስጥ ፅንፈኛ ኃይሎች ጋር ጥምረት በመፍጠር፣ ኢትዮጵያን እያተራመሰ ለመኖር አልሞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አንስተዋል።
የትግራይ ክልል እናቶች በፅንፈኛው የሕወሓት ቡድን ላይ ድንጋይ እየወረወሩ ነው ያሉት ወይዘሮ ኬሪያ፤ የክልሉ ወጣትና ሕዝብም የቡድኑን እኩይ ሴራ በስፋት እየታገለ መሆኑን አስረድተዋል።
ከሻዕቢያ ጋር ከሚፈጽመው የወርቅና የከበሩ ማዕድናት ምዝበራ ባሻገር፣ የትግራይ ወጣቶችን ለሱዳን ጦርነት በመሸጥ የውጭ ምንዛሬ ገቢን የጦር መሣሪያ መግዣ እያደረገ መሆኑን አጋልጠዋል።
በተጨማሪም በፍጹም ጭካኔ ሕፃናትን ከእናት ጉያ በመንጠቅና ወደ ጦር ካምፕ በማጋዝ፣ በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ የሕግ ድንጋጌ የሚያስጠይቅ ሰብዓዊ ግፍ እየፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።
በአሁኑ ወቅትም በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ተቋማትና ዜጎች የሚደርስበትን ውግዘት ጆሮ ዳባ ልበስ በማለት፣ የክልሉን ሕዝብ ወደ ባሰ ጥፋት እየመራው ይገኛል ብለዋል።
የሀገር ሽማግሌዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማትና ሀገራት የቡድኑን እኩይ ሴራ ሊታገሉት እንደሚገባ ተናግረዋል።
የክልሉን ትምህርት ቤቶችም አስቀድሞ በመዝጋትና ወጣቱን ወደ ጦር ካምፕ በማጋዝ የትግራይን ተተኪ ትውልድ እያመከነ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።
የ12ኛ ክፍል ሀገር አቀፍ ፈተናንም "እራሴ አዘጋጃለሁ" በሚል፣ የወጣቱን የነገ ተስፋና ሕልም እያጨለመ መሆኑን አንስተዋል።
ይህም ቡድኑ ሆን ብሎ የትግራይ ክልልን ተተኪ ትውልድ በመዋቅር እያጠፋ እንደሚገኝ ማሳያ ነው ብለዋል።