ቀጥታ፡

የሃይማኖት ተቋማት ለአገር ሰላምና አብሮነት የጀመሩትን ተቀራርቦ የመሥራት በጎ ልምድ ሊያጠናክሩ ይገባል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2 /2018(ኢዜአ) ፦ የሃይማኖት ተቋማት ለአገር ሰላምና አብሮነት የጀመሩትን ተቀራርቦ የመሥራት በጎ ልምድ ሊያጠናክሩ እንደሚገባ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ኸይረዲን ተዘራ (ዶ/ር) አመለከቱ።

የሰላም ሚኒስቴር በህዝቦች መካከል አብሮነትን ማጠናከርና ዘላቂ ሰላም ግንባታን በተመለከተ ከሃይማኖት ተቋማት መሪዎች እና ተወካዮች ጋር ውይይት አካሂዷል።


 

ሚኒስትር ዴኤታው በወቅቱ እንዳሉት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተሰጠውን ተልዕኮ መነሻ በማድረግ እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት ለሰላም ግንባታና ለብሔራዊ መግባባት ያላቸውን አይተኬ ሚና ከግምት ውስጥ በማስገባት በቅርበት እየሠራ ይገኛል።

ይህ ዓይነቱ ትብብርም የሃይማኖት አባቶች በሥነ-ምግባር የታነጸ ትውልድ በመቅረጽ ረገድ የጎላ ድርሻ እንዲወጡና የሕዝቦችን ሰላምና አብሮነት እንዲያጎለብቱ ለማስቻል ያለመ መሆኑንም ገልጸዋል።

መንግሥት የሃይማኖት በዓላት በሰላም ተከብረው እንዲጠናቀቁ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ሚኒስትር ዴኤታው አስገንዝበዋል።

ይህንን ሂደት ይበልጥ ቀልጣፋ ለማድረግም በትኩረት እንደሚሠራም አክለው ተናግረዋል።

መንግሥት ከሃይማኖት ተቋማት ጋር ያለው ግንኙነት ሰላማዊ፣ በመከባበር ላይ የተመሠረተና ሕገ-መንግሥታዊ የሃይማኖትና የመንግሥትን መለያየት መርህ የጠበቀ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።


 

በተቋማቱ መካከል ያለው ሰላምና መልካም ግንኙነት መሻሻሉን ጠቁመው፤ አንዱ ተቋም ከሌላው ጋር በአብሮነትና መደጋገፍ ችግሮቹን ለመፍታት የሚያሳየው አጋርነት እያደገ መምጣቱ የሚበረታታና የሚያስመሰግን መሆኑንም ነው የገለጹት።

ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ለተከታዮቻቸው በአብሮነት፣ በጋራ ተከባብሮ መኖር እና በወሳኝ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ የጀመሩትን ተቀራርቦ የመስራት በጎ ልምድ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አስተላልፈዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የሃይማኖት መሪዎች በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ ሀሳባቸውን አንስተዋል።

ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በቅንጅት መሥራታቸው በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ በጋራ ለመንቀሳቀስ ዕድል መፍጠሩን ገልጸው ይህንን በጎ ሂደት አጠናክረው እንደሚቀጥሉ መናገራቸውን ከሚኒስቴሩ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም