የመንግሥት አዲሱ የቤት ልማት ዕቅድ ለዜጎች ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግሥት አዲሱ የቤት ልማት ዕቅድ ለዜጎች ትልቅ እፎይታ የሚሰጥ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/ 2018(ኢዜአ):-መንግሥት በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ውስጥ በመላ ሀገሪቱ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ መኖሪያ ቤቶችን ለመገንባት ማቀዱ ለዜጎች ትልቅ እፎይታን የሚሰጥ ነው ሲሉ አስተያየታቸውን የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸው፤ የዜጎችን የመኖሪያ ቤት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችሉ ሰፊ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰው፣ የቤት ልማት ጉዳይ ከጉባ ብስራቶች መካከል አንዱ መሆኑንና መንግሥት በከፍተኛ ትኩረት እንደሚሠራበት ተናግረዋል።
በዚህም መሠረት ባለፉት ሰባት ዓመታት ውስጥ ብቻ 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ቤቶች መገንባታቸውን ጠቅሰዋል።
በቀጣዮቹ አምስት ዓመታትም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ቤቶችን በመንግሥት፣ በግል၊ በመንግሥትና በግል አጋርነት እንዲሁም በሌሎች አማራጮች ለመገንባት ዕቅድ ተይዞ ሰፊ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህንን ስኬታማ ማድረግ የሚያስችል አዲስ የመኖሪያ ቤት ፖሊሲ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መጽደቁን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ግንባታውን በገጠርና በከተማ ለማፋጠን በትጋት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል።
በቴክኖሎጂ የታገዘ የግንባታ ፍጥነትን ለመጨመርም እንደ 3ዲ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች ወደ ሥራ እየገቡ መሆኑን ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቤት ልማት ዙሪያ የሰጡትን ማብራሪያ በተመለከተ ኢዜአ ያነጋገራቸው የከተማዋ ነዋሪዎች እንዳመለከቱት፤ ይፋ የተደረገው የቤት ልማት ሥራ ተስፋ ሰጪ መሆኑን ገልጸዋል።
አስተያየታቸውን ከሰጡት ነዋሪዎች መካከል አቶ ተሾመ ረጎ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት ነዋሪዎችን እየፈተነ ያለው የመኖሪያ የቤት አቅርቦት ችግር በዘላቂነት ምላሽ ሊያገኝ ይገባል፡፡
መንግሥት ይህንን ችግር ለመቅረፍ ባለፉት የለውጥ ዓመታት የሰጠው ትኩረትና ያከናወናቸው ተግባራት በርካታ ዜጎችን የቤት ባለቤት ማድረግ የቻለ ቢሆንም፣ አሁንም ቢሆን የችግሩ ስፋት ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ያደረጉት ንግግር መንግሥት የቤት ችግሩን ከመሠረቱ ለመፍታት ያለውን ቁርጠኝነት ይበልጥ ያረጋገጠ በመሆኑ ለነዋሪው ትልቅ ተስፋ የሰጠ ነው ብለዋል።
ሌላኛው የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ መጋቢ ሥርዓት አበራ ግሩም በበኩላቸው፤ አዲስ አበባ የሀገሪቱ ዋና ከተማ እንደመሆኗ መጠን ሰፊ የቤት ልማት ግንባታ እንደሚያስፈልጋት ጠቁመዋል።
ይህንን ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ልዩ ትኩረት መስጠቱ እንዳስደሰታቸው ገልጸው፤ በቀጣይ ሊገነቡ የታሰቡት ቤቶች ለመንግሥት ሠራተኛውና ዝቅተኛ ገቢ ላለው የሕብረተሰብ ክፍል ትልቅ እፎይታ የሚሰጡ በመሆናቸው ግንባታው ሊፋጠን እንደሚገባ ተናግረዋል።
የመዲናዋ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ዝናሽ ተሰማ በበኩላቸው፤ አሁን ያለውን ነባራዊ የመኖሪያ ቤት እጥረት ለመቅረፍ የታቀደው ይህ የቤት ልማት ዕቅድ ለከተማዋ ነዋሪዎች ትልቅ እፎይታ የሚሰጥና የሚያስደስት መሆኑን ተናግረዋል።
መንግሥት በቀጣይ ያቀደው ከ1 ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ቤቶች ግንባታ እጅግ ወሳኝ እርምጃ መሆኑን የጠቀሱት ደግሞ አቶ ማስረሻ አፈወርቅ ናቸው።
የቤት ልማቱ ተደራሽነትና ቀጣይነት እንዲኖረው ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስታውቀዋል።