ቀጥታ፡

የሩዝ ልማት ምርታማነትን በማሳደግ አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ አድርጓል

መቱ ፤ ሐምሌ 2/ 2018(ኢዜአ):- የሩዝ ልማት ስራ ላይ መሳተፋችን  ምርታማነትን በማሳደግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን ለማሳደግ አስችሎናል ሲሉ በኢሉባቦር ዞን የዳሪሙ ወረዳ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

በኢትዮጵያ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ የሩዝ ልማት ስራ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣና አገሪቱ በምግብ ራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረት ውስጥ እንደ አዲስ ስትራቴጂካዊ ሰብል እየታየ ያለ ነው።

መንግስት በአሁኑ ወቅት በተለያዩ አካባቢዎች ለሩዝ ልማት ያለውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም እና በዘርፉ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ከውጭ የሚገባውን ምርት ለመተካት ሰፊ ትኩረት ሰጥቷል ።

በዞኑ የዳሪሙ ወረዳ ቤና 3 ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ኑረዲን ኡስማን፣ አህመድ ሁሴን እና ኢብሳ አሊዩ ለኢዜአ እንዳሉት ፤በኩታ ገጠም ሩዝን በማልማት በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ ባሻገር ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው አድጓል።


 

በተለይ ሜካናይዝድ በሆነ መንገድ የሩዝ ልማቱን በትራክተር እና በኩታ ገጠም እርሻ ለማልማት መቻሉ ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንዳገዛቸው ነው የገለጹት።

ለሩዝ ልማት ስራ ትኩረት በመሰጠቱና ከራሳችን አልፎ ለገበያ የሚቀርብ ምርት በማስገኘቱ በተሻለ መንገድ ተጠቃሚ ለመሆን አስችሎናል ብለዋል።

በቀጣይ ጊዜያትም የሩዝ ልማት ስራውን ከፍ በማድረግ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ በትኩረት እየሰሩ መሆናቸውን  አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።

የዳሪሙ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ታሪኩ ኢታና በበኩላቸው፤ በወረዳው የመኽር እርሻ  128 ሺ ሔክታር መሬት ላይ ሩዝን በማልማት  ከ4 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።


 

በሩዝ ልማቱ ከ172 ሺ በላይ  አርሶ አደሮች የሚሳተፉ ሲሆን  ከ56 ሺህ ኩንታል በላይ የምርት ማሳደጊያ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንደሚውልም ገልጸዋል።

የኢሉባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ አዳሙ ታከለ  በበኩላቸው፤  በዞኑ የግብርና ልማትን ስኬታማ ለማድረግ አርሶ አደሩ በወቅቱ ግብአት  እንዲቀርብለት ከማድረግ  ባለፈ አርሶአደሮች የባለሙያዎች ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል ብለዋል።


 

በመኽሩ ወቅት በሚካሔደው የሩዝ ልማት ስራ 230 ሺ ሔክታር መሬት በማልማት ከ9 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን አንስተዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም