ቀጥታ፡

አዲሱ ስትራቴጂክ ዕቅድ የሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ተልዕኳችንን በገለልተኝነትና በተጠያቂነት ለማከናወን ዳግም ቃል የምንገባበት ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2 /2018(ኢዜአ)፦ አዲሱ ስትራቴጂክ ዕቅድ የሰብአዊ መብቶች ጥበቃ ተልዕኳችንን በገለልተኝነትና በተጠያቂነት ለማከናወን ዳግም ቃል የምንገባበት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቀጣይ አምስት ዓመታት የሚመራበትን ስትራቴጂክ ዕቅድ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዛሬው ዕለት ይፋ አድርጓል።


 

የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ በዚሁ ወቅት፤ ኮሚሽኑ በአዋጅ የተሰጠውን ሰብዓዊ መብቶችን የማስጠበቅ፣የማስፋፋትና የመከታተል ሥልጣንና ኃላፊነት በተሟላ ሁኔታ ለመወጣት እየሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በመሆኑም ባለፉት አምስት ዓመታት በሀገር አቀፍ ደረጃ ሰብዓዊ መብቶች የተጠበቁ፣ የተከበሩና የተሟሉ እንዲሆኑ ለማድረግ ባከናወናቸው ተግባራት አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን በተደረገ ግምገማ ማረጋገጥ መቻሉን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ ከዚህ በፊት ይመራበት የነበረው ስትራቴጂክ ዕቅድ የትግበራ ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ፣ አዲሱ ስትራቴጂክ ዕቅድ ይፋ መደረጉንም አብራርተዋል።

ይህ ስትራቴጂክ ዕቅድ በርካታ አዳዲስ የለውጥ ሐሳቦችን እንዳካተተ በመጠቆም፤ከዚህ በፊት ከነበረው በበለጠ ሁኔታ የሚወጡ ሕጎችና ፖሊሲዎች ሰብዓዊ መብቶችን ያከበሩና የተጣጣሙ እንዲሆኑ ትኩረት ማድረጉን ገልጸዋል።

ዜጎች ከልጅነታቸው ጀምሮ ስለ ሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ግንዛቤ ይዘው እንዲያድጉ ለማድረግም፣የሰብዓዊ መብቶች ትምህርትን በሥርዓተ ትምህርት ውስጥ ለማካተት እንደሚሠራም ጠቁመዋል።

በተጨማሪም በሰብዓዊ መብቶች ጥበቃ ላይ የሚሠራ የጥናትና ምርምር ክፍል እንዲሁም ኢንስቲትዩት ለማቋቋም መታቀዱን ዋና ኮሚሽነሩ ተናግረዋል።

ለዚህም ተግባራዊነት ኮሚሽኑ ከባለድርሻ አካላትና ከዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር በትብብር እንደሚሠራ አረጋግጠዋል።

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል መስፍን እርካቤ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችን ተቀብላ ያጸደቀች ሀገር ናት ብለዋል።


 

ባለፉት አምስት ዓመታት ቋሚ ኮሚቴው ባደረገው ክትትል ኮሚሽኑ ተጨባጭ የሰብዓዊ መብት ጥበቃ ሥራዎችን ማከናወን መቻሉን ማረጋገጥ ተችሏል ነው ያሉት።

በሴቶችና ህጻናት መብቶች፤ በህግ ታራሚዎች አያያዝ፣ በስደተኞች አያያዝ፣ በአካል ጉዳተኞች መብት አጠባበቅ ዙሪያ በርካታ ተግባራት ማከናወኑን አመላክተዋል።

አዲሱ ስትራቴጂክ እቅድ ኮሚሽኑ ስራውን ለማላቅ የሚያስችለው መሆኑን ጠቁመው፤ ቋሚ ኮሚቴው ለስትራቴጅክ እቅዱ መሳካት ክትትልና ድጋፍ በማድረግ የበኩሉን ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።


 

ስትራቴጂክ ዕቅዱ ሰብዓዊ መብቶችን ይበልጥ ለማስጠበቅና የፍትሕ ተደራሽነትን ለማስፋት አይነተኛ ሚና እንዳለው የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ተወካይ ነብይ ተካ ከበደ ናቸው፡፡

ለእቅዱ ተግባራዊነት ሃይማኖት ተቋማት የበኩላቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም