የመንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ግጭትን በዘላቂነት ለማስቆምና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ቁርጠኝነቱን የሚያሳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የመንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ግጭትን በዘላቂነት ለማስቆምና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ቁርጠኝነቱን የሚያሳይ ነው
ገንዳውኃ፣ ሐምሌ 2/2018(ኢዜአ)፡- የመንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ግጭትን በዘላቂነት ለማስቆምና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ቁርጠኝነቱን የሚያሳይ መሆኑን በምዕራብ ጎንደር ዞን የገንዳውሃ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በቅርቡ ለህዝብ ተወካዮች ምክር በሰጡት ማብራሪያ መንግስት ችግሮችን በውይይት ለመፍታት የተያዘውን ጠንካራ አቋም መግለፃቸው ይታወቃል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ለዘላቂ ሰላም፣ ለንግግርና ውይይት መንግስት ሁል ጊዜም ዝግጁ መሆኑን አንስተው የግጭትና ጦርነት እሳቤ አውዳሚና ትርፍ የሌለው ስለመሆኑ ተናግረዋል።
በመሆኑም የመንግስት የሰላም በር ሁልጊዜም ክፍት መሆኑን ገልጸው ሰላምን ለሚመርጡ ሁሉ ለመቀበል ዝግጁ መሆኑን በድጋሚ አረጋግጠዋል።
በአማራ ክልል ምእራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሃ ከተማ ኢዜአ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች የመንግስት የሰላም ጥረትና ቁርጠኝነት የሚደነቅ መሆኑን አንስተዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩም ማብራሪያ መንግስት ለሰላም ያለውን ጠንካራ አቋምና በጥፋት መንገድ ላይ የሚገኙ አካላት ውለው ሳያድሩ እንዲመለሱ እድል የሚሰጥ መሆኑን ገልጸዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ወይዘሮ ትግስት እማኘው፣ ወጣት ገብረኪዳን መንጋው እና አቶ ኪሩቤል መንግስቴ፤ የመንግስት ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ግጭትን በዘላቂነት ለማስቆምና ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ የመፍታት ቁርጠኝነቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።
በተለይም በአማራ ክልል ህዝቡ ዘላቂ ሰላምና ልማት ይፈልጋል ያሉት ነዋሪዎቹ መንግስት ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት የተረጋጋች ሀገር ለመገንባት የሚያደርገው ጥረት የሚደነቅ መሆኑን ገልጸዋል።
የመንግስት የሰላም ጥረት የሀገርና የህዝብ አንድነት ለማጠናከር፣ ሰላምን ለማስፈንና ልማትን ለማፋጠን መሰረት የሚያኖር መሆኑን ነው የተናገሩት።
የመንግስትን የሰላም ጥረት በማገዝና በመደገፍ አካባቢያውን ከጸረ ሰላም ቡድኖች ለመጠበቅ የበኩላቸውን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።