መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ ትውልድ ተሻጋሪ ድንቅ ሥራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ ትውልድ ተሻጋሪ ድንቅ ሥራ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/ 2018(ኢዜአ):-መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ያመጣ ትውልድ ተሻጋሪ ድንቅ ሥራ ነው ሲሉ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ገለጹ።
የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መኩሪያ ኃይሌ (ዶ/ር) ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤ የመንግሥት አገልግሎትን ማሻሻል ለሁለንተናዊ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህንንም ተከትሎ መንግሥት ባለፉት የለውጥ ዓመታት የመንግሥት አገልግሎትን ለማሻሻልና ውጤታማ ለማድረግ፣ በሲቪል ሰርቪሱ ላይ ያተኮሩ በርካታ የለውጥ ተግባራትን በትኩረት እያከናወነ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
በዚህም መሠረት ኮሚሽኑ የሲቪል ሰርቪስ ተቋማትን መገንባት፣ መዋቅርን ማስተካከል፣ በብቃት መቅጠርና ብዝሃነትን ያረጋገጠ የሲቪል ሰርቪስ መፍጠርን ቀዳሚ እርምጃዎች አድርጎ ሲሠራባቸው መቆየቱን ጠቁመዋል።
ከእነዚህ የለውጥ ተግባራት መካከል የአገልግሎት አሰጣጥን ለማሻሻልና ውጤታማ ለማድረግ በቅርቡ ተግባራዊ የተደረገው የ"አንድ መሶብ" አገልግሎት መዋቅር በዋነኝነት የሚጠቀስ መሆኑን ኮሚሽነሩ አንስተዋል።
የባለብዙ አገልግሎት ማዕከል የሆነው የአንድ መሶብ አገልግሎት ከሚያዝያ 18 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ተግባር የገባ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች 106 የመሶብ ማዕከላት መከፈታቸውን አስታውቀዋል።
ከእነዚህ በተጨማሪ ሦስት ተንቀሳቃሽ ማዕከላት እና የተቀናጀ የዲጂታል አገልግሎት መተግበሪያ የተሰኘ የሞባይል አፕሊኬሽን ወደ ሥራ መግባታቸውን ተናግረዋል።
እነኚህ የአገልግሎት መስጫ ማዕከላት ለማኅበረሰቡ ፈጣንና ውጤታማ የሆነ አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
እነዚህ አሠራሮች ወደ ሥራ መግባታቸውን ተከትሎ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ ሥርዓቱ ዜጎች ያለ ምንም እንግልት አገልግሎት የሚያገኙበትን ዕድል በመፍጠሩ በተቋማት ላይ ያላቸው እምነት እየጨመረ መምጣቱን ተናግረዋል።
አገልግሎቱ መሰጠቱን ተከትሎ በተደረገ ዳሰሳ ጥናትም በአሁኑ ወቅት የደንበኞች እርካታ 98 ነጥብ 8 በመቶ መድረስ መቻሉን አስታውቀዋል።
መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ወጪና ጊዜን ከመቀነስ ባለፈ፣ ሠራተኞች ዜጋን በደስታ የሚያገለግሉበትን መነሳሳት የፈጠረ፣ ኢንቨስትመንትን የሚያስፋፋ በመሆኑ እንደ ትውልድ የሚያኮራ ትልቅ ተግባር መሆኑን ገልጸዋል።
የፌደራል ተንቀሳቃሽ መሶብ ማዕከል ተገልጋዮች በበኩላቸው የአንድ መሶብ አገልግሎት ጊዜን ከመቆጠብ ባለፈ የተንዛዛ አሠራርን ያስቀረ ትልቅ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።
በሻይ ዕረፍት ጊዜዬ ብቻ መጥቼ አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ጉዳዬን ማጠናቀቅ ችያለሁ በማለት የአሠራሩን ቀልጣፋነት ያረጋገጡት አቶ መስፍን ተርፋ ናቸው።
አስተያየት ሰጪ አስቻለው ጓዴ በበኩላቸው ቀደም ሲል ከተቋም ወደ ተቋም እየተንከራተቱ የሚያገኙት አገልግሎት አሁን በአንድ ማዕከል ማግኘት መቻላቸው ትልቅ እፎይታ እንደሰጣቸው አስታውቀዋል።
ሌላኛዋ ተገልጋይ ወርቅነሽ እሸቱ አገልግሎቱ ረጅም ሰንሰለቶችን በማስቀረት ሰዓትን፣ ጉልበትንና አላስፈላጊ ወጪን በመቀነስ በአጭር ጊዜ ጉዳዬን እንድፈጽም አስችሎኛል ብለዋል።