ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኃይል የማስተሳሰር ሚናዋን አጠናክራ ትቀጥላለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኃይል የማስተሳሰር ሚናዋን አጠናክራ ትቀጥላለች
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 2 /2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ ቀጣናውን በኃይል የማስተሳሰር ሚናዋን አጠናክራ እንደምትቀጥል የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ገለጹ።
የ22ኛው የምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር አስቸኳይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ይገኛል።
ስብሰባውን አስመልክቶ የውኃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ ኢንጂነር ሱልጣን ወሊ (ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ለጅቡቲ፣ ኬንያ፣ ታንዛኒያ እና ሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ቀጣናዊ ሚናዋን እየተወጣች ነው።
በምሥራቅ አፍሪካ የኃይል ትስስር ማዕቀፍም ሀገሪቱ ቀጣናውን በኃይል የማስተሳሰር ተግባሯን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ይህ የኃይል ትስስር በቀጣናው አስተማማኝ የኃይል አቅርቦት እንዲኖርና ትስስሩን ይበልጥ ለማሳለጥ አስቻይ መድረክ መሆኑንም አንስተዋል።
የኃይል አቅርቦትን በማሳለጥ የተረጋጋ የሕዝቦችን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ማሳደግ ዋነኛው ግባችን ነው ብለዋል።
ለሁለት ቀናት እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ የምክር ቤት ስብሰባ በአባል ሀገራቱ መካከል በጋራ ለመሥራት የተደረጉ ስምምነቶች እና የኤሌክትሪክ አገልግሎት ውሎችን ጨምሮ በተለያዩ አሠራሮች ላይ ውይይት ተደርጎ ውሳኔ ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።
በተጨማሪም የኤሌክትሪክ ገበያ ማዕከል የት ይሁን የሚለው ጉዳይ ሌላው ዋና የውይይት አጀንዳ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል።