ቀጥታ፡

ላሊበላ፦ ከዓለም አቀፍ ቅርስነት እስከ ባህል ዲፕሎማሲ ማዕከልነት

 
በሙሴ መለሰ
 
ከ40 በላይ ኤምባሲዎችን ጨምሮ  ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የተወከሉ ከ70 በላይ ከፍተኛ ዲፕሎማቶችና የልማት አጋሮች ከአፍሪካ እጅግ አስደናቂ ባህላዊና መንፈሳዊ ቅርሶች መገኛ በሆነችው በታሪካዊቷ የላሊበላ ከተማ ከሰሞኑ  ጉብኝት አድርገዋል።  
 
ይህ ታሪካዊ ጉብኝት በዓለም አቀፍ ደረጃ የላሊበላን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የመንከባከብና የመጠበቅ የጋራ ቃልኪዳንን በድጋሚ ለማደስ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።



 
ይህን ዲፕሎማሲያዊ ጉብኝት ያዘጋጀው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ከቱሪዝም ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን፣ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን፣ ከአማራ ክልል መንግሥት፣ ከላሊበላ ከተማ አስተዳደር እና በፈረንሳይ መንግሥት ድጋፍ ከሚንቀሳቀሰው “ዘላቂ ላሊበላ” ፕሮጀክት (Sustainable Lalibela Project) ጋር በመሆን ነው።

ላሊበላ እ.አ.አ በ1978 በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ መዝገብ ላይ የሰፈሩት ድንቅ አብያተ ክርስቲያናትን ይዛለች።  
 
ከስምንት መቶ ዓመታት በፊት (በ13ኛው ክፍለ ዘመን) ከአንድ ወጥ አለት ተፈልፍለው የታነጹት 11ዱ ታሪካዊ አብያተ ክርስቲያናት፤ ዛሬም ድረስ መላውን ዓለም በአድናቆት የሚጎበኛቸው፣ የጥንታዊ ምህንድስና እና የመንፈሳዊነት ጥልቅ መገለጫዎች መሆናቸውን ዩኔስኮ ጉብኝቱን አስመልክቶ ባወጣው ጽሁፍ ላይ አመልክቷል።




 
በጉብኝቱ የተሳተፉት ዲፕሎማቶች  እንደ ቤተ መድኃኔዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ ጊዮርጊስ፣ ቤተ አማኑኤል እና ቤተ ቅዱስ መርቆሬዎስ ያሉትን አብያተ ክርስትያናት ተመልክተዋል።
 
ዲፕሎማቶቹ ላሊበላን “ከዚህ ዓለም ስሪት የላቀ እፁብ ድንቅ ጥበብ” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
 
ቅርሶቹ የጥንታውያኑን አባቶች ድንቅ የምህንድስና ጥበብና የስነ-ህንጻ ልህቀት ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ መሆናቸውን በአድናቆት ተናግረዋል።
 
ዲፕሎማቶቹ ከአብያተ ክርስቲያናቱ ጉብኝት ባሻገር ከነዋሪው፣ ከአካባቢው ማህበረሰብ እና ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት አድርገዋል።



 
ይህ ውይይት ልዑካኑ የላሊበላን ህያው ቅርስ ለመጠበቅ የሚደረጉ ጥረቶችን እና ይህንን ታሪካዊ ስፍራ ለቀጣዩ ትውልድ ለማቆየት እየገጠሙ ያሉ ወቅታዊ ተግዳሮቶችን መፍታት ስለሚቻልበት ሁኔታ በተሻለ መልኩ ለመረዳት አስችሏቸዋል።


 
ጉብኝቱ ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና በቅርቡ በአካባቢው ከተከሰቱ ፈተናዎች በኋላ፣ የላሊበላን የቱሪዝም እንቅስቃሴ መልሶ ለማገገም እና ለማነቃቃት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል።
 
ጎብኚዎቹ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ባህል ሰዎችን በማቀራረብና የእርስ በርስ መግባባትን በማጠናከር ረገድ ስላለው የማይተካ ሚና አጽንኦት ሰጥተዋል።
 
ዩኔስኮ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ወሎ፣ ደቡብ ወሎ እና ከሚሴ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፣ ለፈረንሳይ መንግሥት እና ለጉብኝቱ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋናውን አቅርቧል።
 
ጉብኝቱ የላሊበላን ባህላዊ፣ መንፈሳዊና ኢኮኖሚያዊ ትሩፋቶች እና እሴቶች ባሉበት ለተተኪው ትውልድ ለማሻገር ያለውን ዓለም አቀፍ ቁርጠኝነት ያረጋገጠ መሆኑን ድርጅቱ አመልክቷል።

ዩኔስኮ በቅርሱ አያያዝ፣ ጥበቃ እና ቀጣይነት ላለው አስተዳደር ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት እና ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ቴክኒካዊ ትብብር እና በአቅም ግንባታ  ለበርካታ አስርት አመታት በቅርበት ሲሰራ መቆየቱንና የቅርሱን ዓለም አቀፍ ሀብትነት ጠብቆ ለማቆየት ይህንኑ ተግባሩ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም በጽሁፉ አረጋግጧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም