ቀጥታ፡

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ዋንጫን በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ አነሳ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2 /2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሲዳማ ቡናን 2 ለ 0 አሸንፏል።

ረፋድ ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም በተካሄደው ጨዋታ ጋናዊው አጥቂ ኮንኮኒ ሃፊዝ በ47ኛው እና በየነ ባንጃ በ99ኛው ደቂቃ ግቦቹን አስቆጥረዋል።

ጨዋታውን በርካታ ደጋፊዎች በስታዲየም በመገኘት ተከታትለውታል።

ውጤቱን ተከትሎ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ዋንጫን አንስቷል።

በዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በ46 ነጥብ 16ኛ ደረጃን ይዞ ላጠናቀቀው ወልዋሎ የዛሬው ድል ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ነው።

የኢትዮጵያ ዋንጫ ድሉ በ1948 ዓ.ም ለተመሰረተው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ትልቅ ከሚባሉ ስኬቶች መካከል የሚጠቀስ ነው።

ሲዳማ ቡና በአህጉራዊ ውድድር ተሳትፎውን በማረጋገጡ ምክንያት፣ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ደንብ መሰረት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆኑን ተከትሎ የጨዋታውን ውጤት ሳይጠብቅ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ ኢትዮጵያን ወክሎ በቀጣዩ ዓመት መሳተፉን ማረጋገጡ የሚታወስ ነው።

ተጋጣሚው ሲዳማ ቡና ለተከታታይ ዓመት ለኢትዮጵያ ዋንጫ ቢደርስም ዋንጫውን ለመጀመሪያ ጊዜ የማሸነፍ ህልሙን ማሳከት አልቻለም።

የዘንድሮው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ ሲዳማ ቡና፣ ዓመቱን በሁለት ዋንጫ የማጠናቀቅ ፍላጎቱ ሳይሳካ ቀርቷል።

ሲዳማ ቡና ፕሪሚየር ሊጉን ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነሳ ሲሆን ይህን ተከትሎም በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ መሳተፉን አረጋግጧል።

ሁለቱ ቡድኖች በቀጣዩ ዓመት ኢትዮጵያን በአህጉራዊ የክለብ ውድድሮች ላይ ወክለው ይሳተፋሉ።

በ1937 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ዋንጫ የ80 ዓመት ታሪክ ያለው አንጋፋ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም