ቀጥታ፡

በአሁኑ ወቅት በትግራይ ክልል ያለው የሰብዓዊ መብት ረገጣ ተባብሶ ቀጥሏል-ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/ 2018(ኢዜአ):- ህገ-ወጡ የህወሃት ቡድን የሰላም ስምምነቱን በማፍረስ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ረገጣውን እያባባሰ መምጣቱን የመጀመሪያው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የነበሩት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ገለጹ፡፡

የመጀመሪያው የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ ሴክሬታሪያት ኃላፊ የነበሩት ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ወቅታዊውን የትግራይ ክልል ሁኔታ አስመልክቶ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በአሁኑ ወቅት በክልሉ ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች ሁለንተናዊ እድላቸው እየጠበበና በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ እየገቡ ነው።

ቡድኑ ወጣቶችን በተለያየ መልክ ለጦርነት መማገጃነትና ለውክልና ጦርነት እየተጠቀመባቸው እንደሚገኝም አጋልጠዋል።

የሰብዓዊ መብት ረገጣው ከበፊቱ በበለጠ ሁኔታ እጅግ እየከፋና ጫፍ ላይ መድረሱንም ገልፀው፤ በርካታ ወጣቶች በግድ እየታፈሱ ወደ ማሰልጠኛ ማዕከላት እየተወሰዱ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህም አልፎ ወደ አዲስ አበባ ለመውጣት የሚሞክሩ ተጓዦችን ጭምር በየመንገዱ ከነበሩበት ተሽከርካሪ እያስወረዱ ወደ ስልጠና የሚወስዱበት፣የሚያስሩበትና እስከ ሞት ቅጣት የሚደርስ እርምጃ የሚፈጽሙበት ሁኔታ መኖሩን ጠቅሰዋል።

የቡድኑን ፍላጎት የማይቀበሉ በርካታ ወላጆችም በየአካባቢው ለእስር እየተዳረጉ ይገኛሉ ሲሉ ተናግረዋል።

ታጣቂዎች ወጣቶች ትምህርታቸውን በግድ እንዲያቋርጡ በማድረግ በካምፕ ውስጥ በማሰልጠን ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በዚህም ምክንያት በትግራይ ክልል ውስጥ መደበኛ የልማትና የዴሞክራሲ እንቅስቃሴ ጠፍቶ ህዝቡ ወደ ውጭ ሀገራት እንዲሰደድ እየተገደደ ነው ብለዋል።

ይህ ህዝብን አሸብሮና አስገድዶ ወታደር የማድረግ ዓላማ ከሻዕቢያ የተኮረጀና የተማሩት ትምህርት ነው ያሉት ፕሮፌሰር ክንደያ፤በአሁኑ ወቅት ድርጊቱ በፍጥነትና በስፋት እየተገበረ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በትግራይ ህዝብ ዘንድ ስለ ሰላምና ዴሞክራሲ ሳይሆን ስለ ራሱ ህልውና ብቻ የሚጠይቅበት አስገዳጅ ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁመዋል።

ይህ በትግራይ ክልል ውስጥ ችግር እየፈጠረ ያለው ቡድን በአስቸኳይ ተጠያቂ የሚሆንበት አሰራር ሊዘረጋ እንደሚገባ ፕሮፌሰሩ አሳስበዋል።

መገናኛ ብዙሃን ሰላም እንዲመጣ በትግራይ ክልል ያለውን እውነተኛ ጥፋት ለህዝብ በማጋለጥ በቁርጠኝነት መስራትና መታገል ይኖርባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም