ቀጥታ፡

በአሪ ዞን በዘንድሮ የመኸር እርሻ ከ5 ሚሊዮን በላይ ኩንታል ምርት ይጠበቃል

ጂንካ፤ሐምሌ 2/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አሪ ዞን በዘንድሮ የመኸር እርሻ ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት መታቀዱን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የአሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ የዞኑ ሥነ-ምህዳር ለእርሻ ሥራው ተስማሚ በመሆኑ በተለይ በደጋው አካባቢ ዓመቱን ሙሉ ዝናብ ለማግኘት ያስችላል። 

በቆላማ አካባቢዎች ደግሞ የተለያዩ የውሃ አማራጮችን በመጠቀም የእርሻ ሥራው እንደሚከናወን ተናግረዋል።

በዘንድሮው የመኸር እርሻም ከ46 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በማልማት ከ5 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን ገልጸዋል። 

በዚህም በደጋማው የዞኑ አካባቢ ገብስ፣ ስንዴ፣ በቆሎ፣ ባቄላ እና አተር በስፋት እንደሚመረት ጠቅሰው፤ በቆላማ አካባቢዎች ደግሞ በቆሎ፣ ማሽላ፣ ለውዝ፣ ሰሊጥ፣ ማሾ፣ ጤፍ እና ሱፍ በስፋት እየለማ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

አርሶ አደሩ ኮረሪማ፣ ቡና፣ ዝንጅብል፣ ሱፍ፣ ካሳቫ እና ሌሎች በገበያ ላይ ተፈላጊ የሆኑ ምርቶችን በስፋት በማልማት ተጠቃሚ እንዲሆንም በትኩረት እየተሠራ መሆኑን አስረድተዋል። 

ለእርሻ ሥራው ስኬታማነት በዩኒየኖች አማካኝነት ምርጥ ዘርና የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እየቀረበ መሆኑንም አክለዋል።

በዞኑ የደቡብ አሪ ወረዳ አርሶ አደር ማርቆስ አንክሺ ጥሩ ምርት ያገኙበትን የበልግ ሰብል በማንሳት፣ በአሁኑ ወቅት ማሳቸውን ለመኸር እርሻ እያዘጋጁ መሆኑን ገልጸዋል። 

አስፈላጊውን ግብዓት ተጠቅመው ማሳቸውን እንደሚያለሙና የተሻለ ምርት ለማግኘት እንደሚሠሩም አርሶ አደሩ ተናግረዋል።

ሌላው የወረዳው አርሶ አደር አቶ አዲሱ ፈለቀ በበኩላቸው፤ በዘንድሮው የመኸር እርሻ የተሻለ ምርት ለማግኘት ማቀዳቸውን ገልጸዋል። 

የግብርና ባለሙያዎችም እገዛ እያደረጉላቸው መሆኑን ጠቅሰው፣ የምርጥ ዘርና ማዳበሪያ አቅርቦቱ በወቅቱ እየተከናወነ ነው ብለዋል።

በዘንድሮው የመኸር አዝመራ በቆሎ በስፋት እንደሚያለሙ የጠቆሙት አቶ አዲሱ፤ በተጨማሪም አትክልቶችን በማልማት ተጨማሪ ገቢ ለማግኘት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም