ቀጥታ፡

በክልሉ በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጤናማና አምራች ዜጋን የማፍራት ሥራው ይጠናከራል

ሆሳዕና፤ ሐምሌ 2/2018 (ኢዜአ)፦በማዕክላዊ ኢትዮጵያ ክልል የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህል በማድረግ ጤናማና አምራች ዜጋን ለማፍራትና አብሮነትን ለማሳድግ የተጀመረው ሥራ እንደሚጠናከር የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ።

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሁም የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሠራተኞችና ሃላፊዎች የተሳተፉበት የአካል ብቃት እንቅስቃሴ መርሀግብር ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።


 

የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ሀላፊ አቶ ጌታቸው ሌሊሾ በዚህ ወቅት እንዳሉት በክልሉ የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህል በማድረግ ጤናማና አምራች ዜጋን ለማፍራትና የአብሮነት እሴትን ለማጠናከር እየተሰራ ነው።

በየአካባቢው የሚካሄደው የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ጤናማና አምራች ዜጋ ለማፍራት ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ገልጸው፣ የእርስ በርስ ግንኙነትን በማሳደግ በኩል ፋይዳው የጎላ በመሆኑም ስፖርቱን ለማስቀጠል ይሰራል ብለዋል።

የዛሬው መርሀግብር ስፖርትን ባህል የማድረግ ሥራን ከማጠናከር ባለፈ ወጣቶች በበጎ ፍቃድ ሥራ እንዲሳተፉ ያለመ እንደሆነና መሰል መርሀግብሮችም በየአካባቢው እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የቢሮው ምክትል ሀላፊና የስፖርት ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሰይፈ አለሙ በበኩላቸው እንደገለጹት በስፖርት ልማት ዘርፉ ክልሉ ያለውን አቅም ለይቶ መጠቀም የሚያስችል ሥራ እየተሰራ ነው።

ለእዚህም ደረጃቸውን የጠበቁ  የስፖርት ማዘወተሪያ ስፍራዎችን ለማስፋትና በሁሉም የስፖርት ዘርፍ ታዳጊና ተተኪ ስፖርተኞችን በማፍራት  የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል።

በተያዘው ክረምት ክልሉን የሚወክል የሰርከስ ቡድን ለማቋቋም መታቀዱን የገለጹት ሀላፊው የአካል ብቃት እንቅስቃሴዎችም ብቃት ያላቸው ወጣቶችን ለመለየት አይነተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በአካል ብቃት እንቅስቃሴ ከተሳተፉት የማህበረሰብ ክፍሎች መካከል አቶ ብዙአየሁ ሀይሌ እና አቶ አብድልፈታ ናስር ጤናቸውን ለመጠበቅና የተሟላ ስብዕና ለመገንባት  በአካል ብቃት እንቅስቃሴ በመርሀግብሩ ላይ መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

ስፖርቱ በተለይ የእርስ በርስ ግንኙነታቸውን ከማጠናከር ባለፈ የበጎ ፈቃድ ስራዎችን በጋራ ለማከናወን ምቹ  ሁኔታ እንደተፈጠረላቸውም ገልጸዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ ከተለያዩ መዋቅሮች የተውጣጡ ስፖርተኞችም መሳተፋቸው ታውቋል።

 

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም