ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድና ለቀጣናዊ ደህንነት መረጋገጥ ቁልፍ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላት ሀገር ናት-የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድና ለቀጣናዊ ደህንነት መረጋገጥ ቁልፍ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላት ሀገር ናት-የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 2/2018 (ኢዜአ)፦ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት፣ ለንግድና ለቀጣናዊ ደህንነት መረጋገጥ ቁልፍ ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ ያላት ሀገር መሆኗን የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ።
ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን የሁለትዮሽ አጋርነት ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላቸው አምባሳደሮቹ አንስተዋል።
ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ቆይታ ያደረጉ አምባሳደሮች በሰጡት አስተያየት፤ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን በማሳደግ ረገድ የምታደርገው ጥረት ከጠንካራ የትራንስፖርት ትስስር ጋር ተዳምሮ ቀጣናዊ የማዕከልነት ደረጃዋን አጠናክሮታል ብለዋል።
በኢትዮጵያ የሮማኒያ አምባሳደር ጁሊያ ፓታኪ እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ውህደት እንዲሳለጥ እንዲሁም ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ እየተጫወተች ያለው ሚና የሚደነቅ ነው።
ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፈጣን ዕድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት ግንባር ቀደም መሆኗን የጠቀሱት አምባሳደሯ፤ ነፃ ንግድ እና የገበያ ትስስር በአህጉቱ ያለውን የኢኮኖሚ ልማት ለማፋጠን አስፈላጊ መሆናቸውን አመልክተዋል።
አዲስ አበባ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ መሆኗና ታሪካዊ ሚናዋ ኢትዮጵያን ለዲፕሎማሲ እና የአፍሪካን ተግዳሮቶች ለመፍታት በሚደረጉ የጋራ ጥረቶች ተመራጭ ሀገር እንዳደረጋት አብራርተዋል።
በኢትዮጵያ የኦማን ሚሲዮን መሪ አፍካር አል ፋርሲ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ባላት ሰፊ መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥና በማደግ ላይ ባለው ኢኮኖሚዋ ሳቢያ በቀጣናው ወሳኝ ሀገር ናት ብለዋል።
ቀጣናውን የማስተሳሰር አህጉራዊ ሚናዋ እያደገ ነው ያሉት ሚሲዮን መሪው፤ በአፍሪካ ግዙፉ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለቀጣናዊ እና ለአህጉራዊ ውህደት ትልቅ አስተዋፅኦ አለው ሲሉ ገልጸዋል።
በንግድ እና በኢንቨስትመንት ዙሪያ የኢትዮጵያ እና የኦማን የሁለትዮሽ ግንኙነት እየጎለበተ መምጣቱን ጠቁመው፤ ኦማን የብረት ምርቶችን እና የፕላስቲክ ፓሌቶችን ወደ ኢትዮጵያ ስትልክ፣ ኢትዮጵያ ደግሞ ቡና፣ ሰሊጥ እና ሌሎች የግብርና ምርቶችን ወደ ኦማን እንደምትልክ አስረድተዋል።
በሀገራቱ መካከል ያለውን የንግድ ልውውጥ ይበልጥ ማስፋት የሚቻልበት ዕድል መኖሩን ጠቅሰው፥ ኦማን በተለያዩ መስኮች ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማሳደግ ፍላጎት እንዳላት ጠቁመዋል።
በኢትዮጵያ በሪል ስቴት እና መሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች፣ በአምራች፣ በኮንስትራክሽንና በግብርና ዘርፎች የኦማን ባለሀብቶች ሊሰማሩባቸው የሚችሉባቸው ሰፊ የኢንቨስትመንት አማራጮች መኖራቸውን ጠቅሰዋል።