መንግሥት ለታጠቁ ኃይሎች የሚያቀርበው ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ለሀገር ዘላቂ ሰላም ያለውን ፅኑ ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መንግሥት ለታጠቁ ኃይሎች የሚያቀርበው ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ለሀገር ዘላቂ ሰላም ያለውን ፅኑ ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ ነው
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 2/2018 (ኢዜአ)፦መንግሥት ለታጠቁ ኃይሎች የሚያቀርበው ተደጋጋሚ የሰላም ጥሪ ለሀገር ዘላቂ ሰላም ያለውን ፅኑ ቁርጠኝነት በተግባር የሚያሳይ መሆኑን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ገለፁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በማብራሪያቸውም መንግስት ለዘላቂ ሰላም፣ ለንግግርና ውይይት ሁልጊዜም ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል።
የግጭትና የጦርነት እሳቤ አውዳሚና ትርፍ የሌለው መሆኑን በአሁኑ ወቅት ለሀገር የሚያስፈልገው ሰላም፣ ትብብርና አብሮነት መሆኑን በማብራሪያቸው አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል።
መንግሥት ዛሬም ቢሆን በጫካ ከሚንቀሳቀሱ ታጣቂ ኃይሎች ጋር ለመወያየትና ለሰላም ያለው በር ክፍት መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የሰጡት ማብራሪያ ተከትሎ ኢዜአ ያነጋገርናቸው የመዲናዋ ነዋሪዎች እንደገለጹት፤ መንግስት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ የሚያደርገው ጥረት የሚበረታታ ነው ብለዋል፡፡
ከነዋሪዎች መካከል ተስፋዬ ጸጋዬ እንዳሉት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰላም ዙሪያ የሰጡት ማብራሪያ መንግሥት ለዘላቂ ሰላም መረጋገጥ ያለውን ጽኑ አቋም ያሳየበት ነው።
መንግሥት በጫካ ለሚንቀሳቀሱ የታጠቁ ኃይሎች በተደጋጋሚ የሚያቀርበውን የሰላም ጥሪ ለአብነት አንስተዋል።
በመሆኑም የታጠቁ ኃይሎች ይህንን የመንግሥት ጥሪ በአዎንታ በመቀበል ለዘላቂ ሰላምና ልማት የበኩላቸውን ድርሻ ሊወጡ እንደሚገባ አሳስበዋል።
በተመሳሳይ አቶ ፍቃዱ ንጉሤ፤ የግጭትና የጦርነት እሳቤ አውዳሚና ትርፍ የሌለው መሆኑን በመገንዘብ፣ የታጠቁ አካላት የመንግስትን የሰላም ጥሪ መቀበል እንዳለባቸው አስታውቀዋል።
በልማት የተገኘውን ስኬት ዘላቂ ለማድረግ ዘላቂ ሰላም ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው ለሁለንተናዊ ዕድገትና ለጋራ ተጠቃሚነት መሥራት እንደሚገባ የገለጹት ደግሞ አቶ አስናቀ ለጪሳ ናቸው።
የታጠቁ ኃይሎች መንግሥት ለሰላም የከፈተውን በር በአግባቡ በመጠቀም ለአገር ልማትና ብልጽግና በትጋት መሥራት እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።