በምስራቅ ጎጃም ዞን በክረምቱ ወቅት በሁለት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የፍራፍሬ ልማት ይካሔዳል - ኢዜአ አማርኛ
በምስራቅ ጎጃም ዞን በክረምቱ ወቅት በሁለት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የፍራፍሬ ልማት ይካሔዳል
ደብረ ማረቆስ ፤ሃምሌ 2/2018(ኢዜአ)፡- በምስራቅ ጎጃም ዞን በዘንድሮው ዓመት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ሁለት ሺህ ሄክታር መሬት የሚሸፍን የፍራፍሬ ልማት እንደሚካሔድ የዞኑ ግብርና መምሪያ ገለፀ።
በመምሪያው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ባለሙያ አቶ ተሾመ በላይ ለኢዜአ እንደገለጹት፤በተያዘው ክረምት ለሚካሔደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከአንድ ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኞች ለተከላ ተዘጋጅተዋል።
ለተከላ ከተዘጋጁት ችግኞች ውስጥ የአቮካዶ፣ ብርቱካን ፣ ማንጎ ፣ ሎሚ ፣ ፓፓያ እና የአፕል ዝርያዎች እንደሚገኙበት ነው ያመለከቱት።
የችግኝ ተከላው በሁለት ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የሚካሔድ ሲሆን እስካሁን በተደረገው ጥረት ከ80 ሺህ በላይ የፍራፍሬ ችግኝ መተከሉን ገልፀዋል ።
በዚሁ የፍራፍሬ ችግኝ ተከላ ከ20 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችን እንደሚሳተፉም ነው ያመለከቱት።
በአሁኑ ወቅትም አርሶ አደሩ ከሰብል ልማት ጎን ለጎን በፍራፍሬ ልማት ተሳትፎ ተጠቃሚነቱን እንዲያረጋግጥ የተሻሉ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል።
ለአብነትም ባለፉት ጥቂት ዓመታት ቡናን ጨምሮ ሌሎች የፍራፍሬ አይነቶችን በማልማት አርሶ አደሩ ቋሚ ገቢ በማግኘት ጥሪት እንዲያፈራ እየተደረገ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በየደረጃው ያለው የዘርፉ አመራርና በላሙያም አርሶ አደሩን በመደገፍ እያደረገ ያለው ጥረት የሚበረታታ መሆኑን አስገንዝበዋል።
በዞኑ ባለፉት ዓመታት ጥቂት ዓመት በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በፍራፍሬ ልማት መሸፈኑን ከዞኑ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።