ቀጥታ፡

መንግሥት በየጊዜው የሚያቀርባቸው የሰላም ጥሪዎች ለሀገራዊ መረጋጋት ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ ነው - የሀገር ሽማግሌዎች

ጅግጅጋ፤ ሐምሌ 2/2018(ኢዜአ)፦ መንግሥት በየጊዜው የሚያቀርባቸው የሰላም ጥሪዎች ለሀገራዊ መረጋጋትና ዘላቂ ሰላም  ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች አስታወቁ። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ መስጠታቸው ይታወቃል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸውም መንግስት ለዘላቂ ሰላም፣ ለንግግርና አብሮ ለመስራት ቁርጠኛ መሆኑን በማብራሪያቸው አስረድተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩን ማብራሪያ መሰረት በማድረግ ኢዜአ ያነጋገራቸው የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች፤ መንግሥት በየጊዜው የሚያቀርባቸው የሰላም ጥሪዎች ለሀገራዊ መረጋጋትና ዘላቂ ሰላም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ብለዋል።

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ሱልጣን መሀሙድ ፋረህ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በምክር ቤቱ ያቀረቡት የሰላም ጥሪ መንግሥት ለሀገር ሠላም ያለውን ቁርጠኝነትና ሆደ ሰፊነት የሚያሳይ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ረጅም ታሪክ ያላት ጥንታዊ ሀገር እና የህዝቧም የሰላም እሴት ጠንካራ መሆኑን የጠቀሱት የሀገር ሽማግሌው፤ በሀገሪቱ የሚያጋጥሙ ማናቸውንም አለመግባባቶችና ቅራኔዎች በውይይትና በምክክር መፍታት እንደሚቻል አጽንኦት ሰጥተዋል።

ሰላም ከምንም በላይ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ፤ የሀሳብ ልዩነት ያላቸው አካላት የመንግስትን የሰላም ጥሪ በቅንነት በመቀበል፣ ሀሳብና ጥያቄዎቻቸውን በውይይት መፍታት እንደሚችሉ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ለሁሉም በቂ መሆኗንና ግጭት ልማትን የሚያደናቅፍ መሆኑን ጠቅሰው፤ በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ሰላም እንዲረጋገጥ እያንዳንዱ አካል የመንግስትን የሰላም ጥሪ በመስማትና ወደ ሰላማዊ ህይወት በመመለስ የድርሻውን መወጣት እንዳለበት ገልጸዋል።

ሌላው የአገር ሽማግሌ አቶ አብዲ ኡመር በበኩላቸው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ልዩነቶች በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱና ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት በተደጋጋሚ መግለጻቸው የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል።

በሀገሪቱ አስተማማኝ ሰላምና ልማት እንዲመጣ የሃይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ሊወጡት የሚገባው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አቶ አብዲ አጽንኦት ሰጥተዋል።

የሰላም ጉዳይ የመንግሥት ብቻ ኃላፊነት አለመሆኑን የጠቆሙት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ አቶ አሊ ሙሀመድ ናቸው።

ለሀገር ሰላም መረጋገጥ የሁሉም አካላት ተሳትፎ እንደሚያስፈልግ የገለጹት የአገር ሽማግሌው፤ ተቃርኖ ያላቸው ኃይሎች ሕዝቡን ወደ ችግር ውስጥ ከመክተት ውጭ በጦርነት አሸናፊ የሚሆን አካል እንደማይኖር ተናግረዋል።

በመሆኑም ማናቸውንም አለመግባባቶች በሰለጠነ መንገድና በውይይት የመፍታት ባህል ሊጎለብት እንደሚገባ ገልጸዋል።

መንግሥት የተለያዩ የሀሳብ ነጸብራቆችን በማቀራረብ አካታች የፖለቲካ ምህዳር ለመፍጠር እያደረገ ያለውን ጥረት የጠቀሱት አስተያየት ሰጪው፤ ከጦርነትና ከግጭት የሚገኝ ትርፍ ባለመኖሩ ሁሉም ለሰላም ቅድሚያ ሊሰጥ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም