ቀጥታ፡

የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ ነው

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 2/2018 (ኢዜአ)፦የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የኢትዮጵያን የምግብ ዋስትና የሚያረጋግጥ ተጨባጭ ውጤት እያስገኘ መሆኑን የግብርና ሚኒስቴር ገለጸ።

የግብርና ሚኒስትር ዴኤታ ፍቅሩ ረጋሳ (ዶ/ር) የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ትግበራን አስመልክተው ለመገናኛ ብዙኅን በሰጡት መግለጫ፤ መርሃ ግብሩ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት የኢኮኖሚ አቅም እየፈጠረ ነው።

መርሃ ግብሩ የአርሶና አርብቶ አደሩን የምግብና ሥርዓተ-ምግብ ዋስትና ከማረጋገጥ ባሻገር፣ የከተሞችን የእንስሳት ተዋጽኦ ምርቶች የገበያ ፍላጎት በማሟላት ጉልህ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

የዜጎችን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ያለው የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር የምግብ ዋጋ ንረትን በመቆጣጠር ረገድም ከፍተኛ ጠቀሜታ እያስገኘ መሆኑን አስረድተዋል።

የእንስሳት ሀብት ምርታማነትን በማሻሻል በኩልም፤ የወተት ላም ዝርያ ማሻሻልን ጨምሮ በዶሮና እንቁላል ምርት ዘርፍ ለወጣቶችና ለሴቶች በርካታ የሥራ ዕድሎችን መፍጠሩን አንስተዋል።

ለአብነትም የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከመጀመሩ በፊት በዓመት ይሰራጭ የነበረው 26 ሚሊየን የዶሮ ጫጩት ብቻ የነበረ ቢሆንም ዘንድሮ ግን ወደ 184 ሚሊዮን ማደጉን አስታውቀዋል።

ለውጭ ገበያ የሚቀርብ የስጋ ምርትን ለማሳደግ የተከናወኑ ዘመናዊ የከብት ማደለብ ስራዎችና የእንስሳት ክትባት ተደራሽነት መሻሻሎች፣የዘርፉን የኤክስፖርት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ እንዳሳደጉት አብራርተዋል።

ከዚህ ባሻገርም የኩሬ ዓሣ እርባታን በማስፋፋትና በዘመናዊ የንብ ማነብ ሥርዓት የዜጎችን የአመጋገብ ሥርዓትና የምርታማነት ባህል በማሳደግ የውጭ ምንዛሬን የሚያስገኝ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም