ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 8 ሺህ 961 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ተደርጓል

አሶሳ፤ ሐምሌ 2/2018 (ኢዜአ)፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 8 ሺህ 961 ኪሎ ግራም ወርቅ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ ሀገሪቱ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከወርቅ ማዕድን ዘርፍ 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር ታሪካዊ ገቢ ማስመዝገቧን ይፋ አድርገዋል።

መንግስት ህገ-ወጥ የወርቅ ዝውውርና ኮንትሮባንድን በመከላከልና አምራቾችን በማበረታታት የወርቅ ግዥ ሥርዓትና የዋጋ ማሻሻያ ማድረጉ ይታወሳል። 

በማዕድን ዘርፍ የተደረገው የፖሊሲ ማሻሻያ እና ድጋፍ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት ማስቻሉንም አስታውሰዋል።

የማዕድን ሀብት ክምችት ከሚገኝባቸው አካባቢዎች አንዱ የሆነው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ከለውጡ ወዲህ ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት  የማዕድን ምርት ዕድገት በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል።

የክልሉ ማዕድን ሀብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ናስር ሙሐመድ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ መንግስት ለማዕድን ዘርፍ የሰጠው ትኩረት ዘርፉ የሀገር ኢኮኖሚ በመደገፍ ለበርካታ ዜጎች የስራ ዕድል እንዲፈጥር አስችሎታል።

በክልሉ ወርቅን ጨምሮ በርካታ ማዕድናትን በማልማት የአካባቢውን ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የገለጹት ኃላፊው፤ ክልሉ ከዘርፉ የሚያገኘው ገቢም በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱን አስታውቀዋል።

ለአብነትም በ2018 በጀት ዓመት 8 ሺሕ 961 ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ መግባቱን ገልጸው፤ ለስኬቱም መንግሥት በዘርፉ የወሰደው የፖሊሲ ማሻሻያ ለአምራቾች የፈጠረው ምቹ ሁኔታ ቀጥተኛ አስተዋጽኦ ማድረጉን ተናግረዋል።

ዘርፉ ለክልሉ የገቢ አቅም መጠናከር ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን እና በበጀት ዓመቱ ቢሮው ከ246 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ ከዘርፉ ማግኘቱን ገልጸዋል።

በክልሉ በተለይም አነስተኛ የወርቅ አምራቾች ቴክኖሎጂን በመጠቀም ወርቅን በዘመናዊ መልኩ ማምረት ከጀመሩ ወዲህ በዘርፉ የሚታየው ውጤት እየጨመረ መምጣቱን ገልጸዋል።

በክልሉ ከወርቅ በተጨማሪ ግራናይት፣ ድንጋይ ከሰል፣ እምነበረድ እና ሌሎች ማዕድናትን ለማልማት የሚያስችሉ ተግባራት በመከናወን ላይ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ዘርፉ ለሀገር ኢኮኖሚ ያለውን አበርክቶ አጠናክሮ በማስቀጠል ሁሉንም ማዕድናት ጥቅም ላይ ማዋል ይገባል ብለዋል።

በዘርፉ የሚሠማሩ ወጣቶችም በተግባር የታገዘ ስልጠና ወስደው የማዕድን ስረው ላይ እንዲሰማሩ በማድረግ ውጤታማ ስራ በመከናወን ላይ መሆኑን አብራርተዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም