በጠመንጃ አፈሙዝ ስልጣን ለመያዝ መሞከር ጊዜው ያለፈበት ኋላ ቀር እሳቤ ነው-የአብን ምክትል ሊቀመንበር - ኢዜአ አማርኛ
በጠመንጃ አፈሙዝ ስልጣን ለመያዝ መሞከር ጊዜው ያለፈበት ኋላ ቀር እሳቤ ነው-የአብን ምክትል ሊቀመንበር
ባህር ዳር፤ሐምሌ 2/2018 (ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ በጠመንጃ አፈሙዝ ስልጣን ለመያዝ መሞከር ጊዜው ያለፈበት ኋላ ቀር እሳቤ መሆኑን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር መልካሙ ፀጋዬ ገለጹ።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ ስርአት ተለውጦ አካታችና አሳታፊ በመሆኑ በሀገሩ ጉዳይ ላይ ሁሉም በእኩልነት የሚሳተፍበት ምቹ የፖለቲካ ምህዳር ተፈጥሯል።
በኢትዮጵያ አጋር ተብለው የዳር ተመልካች የነበሩ ክልሎች አሁን ላይ እኩል ተሳታፊ ሆነው በሀገራቸው ጉዳይ ላይ እየወሰኑ ነው።
በውጭና በሀር ውስጥ መሰረታቸውን አድርገው በትጥቅ ትግል ውስጥ የነበሩ ወገኖችም የለውጡ መንግስት የፈጠረውን ምቹ መደላድል ተጠቅመው በሰላማዊ ትግል ቀጥለዋል።
የፖለቲካ ስርአቱ በዴሞክራሲያዊ የምርጫ ሂደት እየዳበረ በኢትዮጵያ ጠንካራ ሀገረ መንግስት የመገንባት ስራም በመከናወን ላይ ይገኛል።
እነዚህን መልካም እድሎች በመግፋት በጠመንጃ ለጥያቄያችን መልስ እናገኛለን፤ አሸንፈንም ስልጣን እንይዛለን በማለት በጫካ የሚንቀሳቀሱ ጽንፈኞች ይስተዋላሉ።
በመሆኑም በዚህ ዘመን በኢትዮጵያ ከሰላማዊ የትግል ስልት ውጭ የትኛውም አይነት የሀይል እንቅስቃሴ አክሳሪና የማያዋጣ መሆኑን የአማራ ብሄራዊ ንቅናቄ (አብን) ምክትል ሊቀመንበር መልካሙ ፀጋዬ ገልጸዋል።
በዚህ ዘመን በምክክር ችግሮችን የመፍታት እና በምርጫ ተወዳድሮ የማሸነፍ ሰፊ እድል እያለ በጫካ የሚደረግ የጠመንጃ እንቅስቃሴ በፍፁም ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ፓርቲያችን በፅኑ ያምናል ብለዋል።
በኢትዮጵያ በጠመንጃ ስልጣን ለመያዝ መሞከር ጊዜው ያለፈበት ኋላ ቀር እሳቤ በመሆኑንም ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የሃይል አማራጮችን በመተው በመቀራረብ በምክክር የቆዩ ሀገራዊ ችግሮችን ለመፍታት የሁላችንም ዝግጁነትና ቁርጠኝነት ያስፈልጋል ብለዋል።
በተቃርኖ የከረሩ ዋልታ ረገጥ እሳቤዎችን በማለዘብ በምክክር ወደ መሀል በማምጣት ለችግሮቻችን ዘላቂ መፍትሄ ልናበጅ ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘውን ሀገራዊ የምክክር እድል መጠቀም የትውልድንና የሀገርን ቀጣይ እጣ ፋንታ መወሰን ይገባናል ብለዋል።
በሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ የተለዩ አጀንዳዎች የዜጎችን የዘመናት ጥያቄዎች ጭምር ማእከል ያደረጉ በመሆኑ ለስኬታማነቱ መስራት የሁላችንም ሃላፊነት ነው ሲሉ አቶ መልካሙ ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ሀገራዊ ምክክሩ የሁሉንም ሃሳብ ለማካተት ጥረት የተደረገበት መሆኑን አንስተው እድሉን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ማለታቸው ይታወሳል።