ቀጥታ፡

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረና ለጠንካራ ዴሞክራሲ መሠረት የጣለ ነው-ምሁራን

ቦንጋ ፤ ሀምሌ 2 /2018 (ኢዜአ)፦ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረና ለጠንካራ ዴሞክራሲ መሠረት የጣለ መሆኑን ምሁራን ገለፁ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባቀረቡት ምላሽና ማብራሪያ፣ የዘንድሮው ምርጫ ከተለመደው የፖለቲካ ፉክክር ባለፈ ጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት ልምምድ የታየበት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል።

ምርጫው እንዳይካሄድ በሚፈልጉ ኃይሎች ከፍተኛ ጫና ሲደርስ እንደነበር የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሕዝቡ እነዚህን ማስፈራሪያዎችና ጫናዎች ወደ ጎን በመተው እስከ እኩለ ሌሊት ድምፁን በመስጠት ፍላጎቱን በግልጽ ማሳየቱን ተናግረዋል።

ብልጽግና ፓርቲ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ሲል፣ 15 በመቶ የሚሆነውን የምክር ቤት ወንበር ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻቸውን እንዲወዳደሩበት ማድረጉንና ይህም በርካታ ፓርቲዎች ፓርላማ እንዲገቡ ዕድል መፍጠሩን አብራርተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ማብራሪያና በ7ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የዘርፉ ምሁራን በበኩላቸው፤ ምርጫው የኢትዮጵያን ፖለቲካ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋገረና ለጠንካራ የዴሞክራሲ ሥርዓት መሠረት የጣለ መሆኑን ገልጸዋል።

የቦንጋ ትምህርት ኮሌጅ የስነ-ዜጋና ሥነ-ምግባር ምሁር መሐመድ ናጂ እስማኤል፤ 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ እስካሁን ከተደረጉ ምርጫዎች በተለየ መልኩ አሳታፊ፣ ዴሞክራሲያዊ፣ ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ ድምፁን የሰጠበትና ሰላማዊ እንደነበር ተናግረዋል። 

ይህም የውጭና የሀገር ውስጥ ታዛቢዎች የመሰከሩት ሃቅ መሆኑን ጠቁመው ገዢው ፓርቲ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በሰጠው ትኩረት የፖለቲካ ምሕዳሩ በመስፋቱ የተገኘ መሆኑን አስረድተዋል።

በምርጫው ብልጽግና ፓርቲ 15 በመቶ መቀመጫዎችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ብቻቸውን እንዲወዳደሩበት ማድረጉ፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ከ"እኔ ብቻ" እሳቤ ተላቆ ወደ ትብብር መሻገሩን የሚያሳይ እርምጃ መሆኑን አመልክተዋል። 

ይህም የሚመሠረተው መንግሥት አካታችና በርካታ ድምፆች የሚሰሙበት እንዲሆን ዕድልን እንደሚፈጥርም አስረድተዋል።

የዘንድሮው ምርጫ በርካታ ዜጎች ድምፅ የሰጡበት፣ 42 የፖለቲካ ፓርቲዎች የተሳተፉበት፣ በቴክኖሎጂ የታገዘና ጠንካራ ትብብር ጎልቶ የታየበት መሆኑ ኢትዮጵያ ወደ አዲስ የዴሞክራሲ ምዕራፍ መሻገሯን የሚያሳይ ነው ያሉት ደግሞ በኮሌጁ የስነ-ምግባርና ሥነ-ዜጋ መምህር እንግዳ ገብረማርያም ናቸው።

ከወትሮ በተለየ መልኩ ሕዝቡ ጫናዎች ሳይበግሩት በነቂስ ወጥቶ ያስተዳድረኛል ያለውን መምረጡ ለዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ያለውን ፍላጎት ያሳየበትና ለመንግሥትም ትልቅ የቤት ሥራ የሰጠበት መሆኑን ተናግረዋል። 

አብላጫውን መቀመጫ ብልጽግና ፓርቲ ቢያገኝም፣ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችም በተፈጠረው ምቹ ሁኔታ መቀመጫ ማግኘታቸው በቀጣይ በፓርላማም ሆነ በክልል ምክር ቤቶች የተለያዩ ሐሳቦች እንዲንሸራሸሩ ዕድል መፍጠሩን ጠቁመዋል። 

ይህም በጋራ የመስራት ባህል እንዲጎለብት በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ደረጃ እንደሚያሻግራት ገልጸው የሚመሠረተውን መንግሥት በተሳትፎ እንዲጠነክር እንደሚያደርገውም አመልክተዋል።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም