ቀጥታ፡

ለቡና ልማት በተሰጠው ትኩረት የተመዘገበው ስኬት በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሯል

ሮቤ፤ ሐምሌ 2/2018(ኢዜአ)፦መንግስት ለቡና ልማት በሰጠው ትኩረት የተመዘገበው ስኬት የኢክስፖርት ገቢን ከማሳደግ ባለፈ በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮች ትልቅ መነሳሳትን መፍጠሩን በባሌ ዞን የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 30ኛ መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኝተው፣ የ2018 በጀት ዓመት የመንግሥት አፈጻጸምን በተመለከተ ከምክር ቤት አባላት ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ማብራሪያ ለቡና ልማት የተሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ኢትዮጵያን በዓለም ሦስተኛዋ ቡና ላኪ ሀገር እንድትሆን ማስቻሉን ገልጸዋል። 

አክለውም ሀገራዊ የሪፎርም ሥራው ለውጭ ምንዛሬ ግኝት ስኬቶች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

በዚህም በዘንድሮው ዓመት ኢትዮጵያ ከሸቀጦች ኤክስፖርት ያገኘችው ገቢ ከ11 ቢሊዮን ዶላር በላይ መሆኑን ገልጸው፣ ከቡና ኤክስፖርት ብቻ በዓመቱ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያ የኮፊ አራቢካ መገኛ እንደመሆኗ መጠን በየትኛውም ዘመን ቡና ወደ ውጭ ስትልክ መቆየቷን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ከለውጡ ዓመታት በፊት ግን ይህ ነው የሚባል ገቢ ማግኘት እንዳልተቻለ አስታውሰዋል። 

በዚህም ሀገሪቱ ባለፉት 17 ዓመታት ቡናን ወደ ውጭ በመላክ በአጠቃላይ ያገኘችው ገቢ 3 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር ብቻ እንደነበር ገልጸው፤ መንግሥት ለቡና ልማት በሰጠው ከፍተኛ ትኩረት ግን በዘንድሮው ዓመት ብቻ 3 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢን ማሳካት መቻሉን አነጻጽረው አብራርተዋል።

በዚሁ ጉዳይ ላይ ኢዜአ ያነጋገራቸው የባሌ ዞን የግብርና ጽሕፈት ቤት አመራሮችና ባለሙያዎች እንዳሉት፤ መንግሥት ለቡና ልማት በሰጠው ትኩረት የተመዘገበው ስኬት በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶና አርብቶ አደሮች ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሯል።


 

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ሙአዊያ ፉአድ፤ በዞኑ ባለፉት ዓመታት ለቡና ልማት በተሰጠው ትኩረት ተጨባጭ ለውጥ መመዝገቡን በማሳያነት አንስተዋል። 

በዞኑ ከለውጥ ዓመታት በፊት በቡና ልማት የተሸፈነው መሬት ከ40 ሺህ ሄክታር እንደማይበልጥ ጠቅሰው፣ ከለውጡ ወዲህ ግን ልማቱን ወደ 78 ሺህ ሄክታር ማሳደግ መቻሉን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ከአንድ ሄክታር የሚገኘውን የቡና ምርታማነት ከአምስት ኩንታል ወደ 10 ነጥብ 1 ኩንታል ማሳደግ መቻሉም የዘርፉ ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል። 

ይህ ውጤት ሊገኝ የቻለው አርሶ አደሩ ያረጁ የቡና ተክሎችን በመጎንደልና ነቅሎ በአዲስ ምርጥ ዝርያ በመተካቱ መሆኑንም ጠቁመዋል።


 

የቡና ልማትን ለማስፋፋት በተሰጠው ትኩረት በየዓመቱ የሚተከለውን የቡና ችግኝ ከ15 ሚሊዮን ወደ 42 ሚሊዮን ማሳደግ መቻሉን የገለጹት ደግሞ በጽሕፈት ቤቱ የቡና፣ አትክልትና ቅመማ ቅመም ልማት ቡድን መሪ አቶ ወንደሰን ነጋ ናቸው።

በዚህም የዞኑ ዓመታዊ የቡና ምርት ከ15 ሺህ ቶን ወደ 44 ሺህ ቶን ማድረስ መቻሉ በዘርፉ ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል ተጠቃሽ መሆኑን አመልክተዋል።

በቀጣይም የቡና ልማትን ይበልጥ ለማስፋፋትና በሄክታር የሚገኘውን ምርታማነት ከ21 ኩንታል በላይ ለማድረስ፣ በቴክኖሎጂ የታገዘ ሥራን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ኢኒሼቲቭ ተቀርጾ ወደ ሥራ መገባቱን አክለዋል።

አስተያየት ሰጪዎቹ በማጠቃለያቸው፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ ላይ ለቡና ልማት የተሰጠው ትኩረት ኢትዮጵያን በዓለም ሦስተኛዋ ቡና ላኪ ሀገር እንድትሆን ማስቻሉን መግለጻቸው ትልቅ እምርታ መሆኑንና በዘርፉ ለተሰማሩ አርሶ አደሮችም የበለጠ የሥራ መነሳሳትን እንደሚፈጥርም ገልጸዋል።

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም