ቀጥታ፡

ፈረንሳይ ከሞሮኮ፦ ማን ወደ ግማሽ ፍፃሜው ያልፋል?

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2/2018 (ኢዜአ)፦ የ23ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ ከእንድ ቀን እረፍት በኋላ ዛሬ በሩብ ፍጻሜ መርሐ ግብር ይመለሳል።

ምሽት አምስት ላይ ፈረንሳይ ከሞሮኮ በቦስተን ስታዲየም የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።

ፈረንሳይ በ16ቱ የጥሎ ማለፍ መርሐ ግብር ፓራጓይን በመርታት በዓለም ዋንጫ ተሳትፎ ታሪኳ ለ10ኛ ጊዜ ወደ ሩብ ፍጻሜው ገብታለች።

ተጋጣሚዋ ሞሮኮ ከዓለም ዋንጫው አዘጋጅ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችውን ካናዳን 3 ለ 0 አሸንፋለች።

ሞሮኮ በዓለም ዋንጫው ታሪክ ሁለት ጊዜ ሩብ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያዋ ሀገር ሆናለች።

ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም በዓለም ዋንጫው አንድ ጊዜ ተገናኝተዋል።

ኳታር እ.አ.አ በ2022 ባዘጋጀችው 22ኛው የፊፋ ዓለም ዋንጫ በግማሽ ፍጻሜው ተገናኝተው ፈረንሳይ 2 ለ 0 አሸንፋለች።

ቴዎ ሄርናንዴዝ እና ራንዳል ኮሎ ሙዋኒ በወቅቱ ግቦቹን ያስቆጠሩ ተጫዋቾች ናቸው።

ሞሮኮ በጨዋታው ሽንፈት ቢገጥማትም በዓለም ዋንጫ ታሪክ ግማሽ ፍጻሜ የገባች የመጀመሪያ ሀገር በመሆን ታሪክ ሰርታለች።

ሁለቱ ሀገራት በአጠቃላይ በውድድር እና በወዳጅነት ጨዋታዎች ላይ ስድስት ጊዜ ተገናኝተዋል።

ፈረንሳይ አራት ጊዜ በማሸነፍ የበላይነቱን ይዛለች። ሞሮኮ አንድ ጊዜ ስታሸንፍ በቀሪ አንድ ጨዋታ አቻ ተለያይተዋል።

ሞሮኮ በታሪኳ ፈረንሳይን ማሸነፍ የቻለችው አንድ ጊዜ ብቻ ሲሆን እሱም እ.ኤ.አ. በ1998 በንጉሥ ሀሰን ሁለተኛ ዋንጫ ላይ ሁለት እኩል ተለያይተው በፍጹም ቅጣት ምት 6 ለ 5 ያሸነፈችበት ጨዋታ ነበር።

በነዚህ ስድስት ጨዋታዎች ላይ ፈረንሳይ 14 ጎሎችን ስታስቆጥር፣ ሞሮኮ 7 ግቦችን ከመረብ ላይ አሳርፋለች።

የዓለም ዋንጫውን ታነሳለች ተብላ ሰፊ ግምት ያገኘችው ፈረንሳይ የማጥቃት ኃይሏ ለተጋጣሚዎቿ የራስ ምታት ሆኗል።

የ27 ዓመቱ ኪሊያን እምባፔ በዘንድሮው ውድድር 7 ግቦችን በማስቆጠር እና ሁለት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ተመሳሳይ የግብ መጠን ያለውን አርጀንቲናዊውን ሊዮኔል ሜሲ በመብለጥ የኮከብ ግብ አግቢነቱን እየመራ ይገኛል።

ምባፔ በዓለም ዋንጫው በአጠቃላይ 19 ግቦችን ከመረብ ላይ ያሳረፈ ሲሆን ከምንጊዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪው ሜሲ (20 ጎሎች) በአንድ ግብ ዝቅ ብሎ ይገኛል።

ማይክል ኦሊሴ በዘንድሮው የዓለም ዋንጫ አምስት ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን በማቀበል ድንቅ ብቃቱን እያሳየ ይገኛል።

በሞሮኮ በኩል ሶስት ግቦችን በዓለም ዋንጫው ያስቆጠረው የ25 ዓመቱ አጥቂ ኢስማኤል ሳይባሪ ከካናዳ ጋር በነበረው ጨዋታ ባጋጠመው የጡንቻ መሳሳብ ጉዳት ከዛሬው ጨዋታ ውጪ ሆኗል።

የሳይባሪን ቦታ ሶፊያን ራሂሚ በዛሬው ጨዋታ እንደሚሸፍን ይጠበቃል።

በዓለም ዋንጫው በተመሳሳይ ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩት አዜዲን ኡናሂ እና ሶፊያን ራሂሚ የማጥቃት እንቅስቃሴውን በዋነኛነት ይመሩታል።

ምርጥ ጓደኛማቾች እየተባሉ የሚጠሩት አሽራፍ ሀኪሚና ኪሊያን እምባፔ በጨዋታው ላይ የሚኖራቸው ፉክክር ተጠባቂ ሆኗል።

ፈረንሳንይ ጨዋታውን የማሸነፍ የቅድሚያ ግምት ብትወስድም ሞሮኮ ጠንካራ ተፋላሚነቷን ታሳያለች ተብሎ ይጠበቃል።

የዛሬው ጨዋታ አሸናፊ በግማሽ ፍጻሜው ከስፔን እና ቤልጂየም አሸናፊ ጋር ይገናኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም