ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ ዋንጫን ማን ያነሳል?  ሲዳማ ቡና ወይስ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ?

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 2 /2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዋንጫ የፍጻሜ ጨዋታ በሲዳማ ቡና እና ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ መካከል ዛሬ ይደረጋል።

ጨዋታው ከረፋዱ አምስት ሰዓት ላይ በአዲስ አበባ ስታዲየም ይካሄዳል።

በግማሽ ፍጻሜው ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ መድንን፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ መቀሌ 70 እንደርታን በተመሳሳይ በመለያ ምት አሸንፈዋል።

ሲዳማ ቡና ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ደርሷል።

ቡድኑ ባለፈው ዓመት ውድድሩን አሸንፎ የነበረ ቢሆንም ቅጣት የተጣለባቸውን ተጫዋቾችን በፍጻሜው ላይ በመጠቀሙ ምክንያት ዋንጫው ለወላይታ ድቻ መሰጠቱ የሚታወስ ነው።

ሲዳማ ቡና ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ዋንጫ ለማንሳት ይፋለማል።

ተጋጣሚው ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ለኢትዮጵያ ዋንጫ ፍጻሜ ሲያልፍ የአሁኑ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ሁለቱ ክለቦች በዘንድሮው የውድድር ዓመት ሲገናኙ የአሁኑ ለሶስተኛ ጊዜ ነው።

በሊጉ ባደረጓቸው ሁለት ጨዋታዎች ሲዳማ ቡና አንድ ጊዜ ሲያሸንፍ በቀሪው መርሐ ግብር አቻ ተለያይተዋል።

ቡድኖቹ በሊጉ የመጀመሪያ ሳምንት ተገናኝተው ሲዳማ ቡና 4 ለ 1 ማሸነፉ አይዘነጋም።

በወቅቱ በነበረው ጨዋታ አበባው አጂሶ፣ አስቻለው ሙሴ፣ ተመስገን መንገሻ እና የወልዋሎው ጌታሁን ባፋ በራሱ ላይ ግቦቹን ከመረብ ላይ አሳርፈዋል። ሰመረ ሀፍታይ ለወልዋሎ ብቸኛውን ጎል ከመረብ ጋር አገናኝቷል።

በ20ኛ ሳምንት ባደረጉት ጨዋታ ደግሞ ያለ ግብ አቻ ተለያይተዋል።

ሲዳማ ቡና የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነሳ ሲሆን ይህን ተከትሎም በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ መሰታፉን አረጋግጧል። ቡድኑ የውድድር ዓመቱን በሁለት ዋንጫ ለመደምደም ዛሬ ወደ ሜዳ ይገባል።

ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የዘንድሮውን የውድድር ዓመት በ46 ነጥብ 16ኛ ደረጃን በመያዝ አጠናቋል።

ሲዳማ ቡና በአህጉራዊ ውድድር  ተሳትፎውን በማረጋገጡ ምክንያት፣  በኢትዮጵያ  እግር ኳስ ፌዴሬሽን የውድድር ደንብ መሰረት ወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የፍጻሜ ተፋላሚ መሆኑን ተከትሎ   የጨዋታውን ውጤት ሳይጠብቅ በቀጥታ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ላይ መሳተፉን አረጋግጧል።

ሁለቱም ቡድኖች ታሪካዊውን የኢትዮጵያ ዋንጫ ለማንሳት ይፈለማሉ።

በ1937 ዓ.ም የተጀመረው የኢትዮጵያ ዋንጫ የ80 ዓመት ታሪክ ያለው አንጋፋ ውድድር ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም